በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ወባ በኢትዮጵያ


የወባ ሥርጭትና ሞት ከሃምሣ ከመቶ በላይ መቀነሱ ተነገረ፡፡

በአውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2000 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተከናወኑ ተግባራት የመነደፍንና የሞትን መጠን ከሃምሣ ከመቶ በላይ መቀነስ መቻሉን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወባ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራም ዋና ተጠሪ ገለፁ፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ከትናንት በስተያ ባወጣው አዲስ ሪፖርቱ ባለፉት አሥር ዓመታት በዓለም ዙሪያ በወባ ላይ የተጨበጠው ድል አበረታች መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡ ወባ ከተስፋፋባቸው 43 የአፍሪካ ሃገሮች በአሥራ አንዱ የመያዝና የሞት መጠን ከሃምሣ ከመቶ በታች ቀንሶ እንደነበር አመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከ2005 ዓ.ም በፊት በነበረው ጊዜ እጅግ የተስፋፋ የወባ ወረርሽኝ ብዙውን የሃገሪቱን ክፍል አዳርሶ እንደነበር ተጠሪው አቶ መሠረት አሠፋ አስታውሰው 75 ከመቶ የሚሆነው ክልል ወባ የሚገኝበትና ለመስፋፋትና ለመራባትም አመቺ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመከላከሉ ሥራ ውስጥም ለ45 ሚሊየን ሕዝብ አጎበር መሠራጨቱን፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ከምርመራ እስከ ሕክምና አገልግሎት በቀበሌ ደረጃ እንደሚሠጡ፣ ለወባ መስፋፋት አመቺ የሆኑ አካባቢዎችን እየተከታተሉ እንደሚያፀዱና አስፈላጊ የቤት ውስጥ ርጭት እንደሚያካሂዱና ትምህርትም እንደሚሠጡ አቶ መሠረት ገልፀዋል፡፡

በዚህም የመነደፉ መጠን በ54 ከመቶ እና የወባ ሞት መጠን ደግሞ በ55 ከመቶ መቀነሱን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG