የእርዳታ ጠባቂው ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረው በብዙ መውረዱ ቢገለፅም የምግብ እጥረቱ አርባ ከመቶ የሚሆነው የተከሰተው በሰላም እጦት ተቸግሮ በሚገኘውና የተበታተነ የሕዝብ አሠፋፈር ባለበት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መሆኑ ሪፖርተራችን ፒተር ሃይንላይን ከአዲስ አበባ የላከው ዘገባ ጠቁሟል፡፡
ባለፈው ዓመት እንዲህ ዓይነቱ አጣዳፊ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው ቁጥር 5 ነጥብ 2 ሚሊየን የነበረ ሲሆን ለዚህ መሻሻል ቁልፍ አስተዋፅዖ አበርክተዋል ያሏቸውን ሁለት ሁኔታዎች የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ምትኩ ካሣ ጠቁመዋል፡፡
አንዱ ጥሩ የአየር ሁኔታ የነበረ መሆኑ ሲሆን በዚህ ምክንያት ከአምስት ዜጎቿ አራቱ የዕለት ሕይወታቸው በግብርና ላይ በተመሠረተባት ኢትዮጵያ ዘንድሮ አዝመራው ሠምሮ ሰብሉ በጥሩ ሁኔታ ተሰብስቧል፡፡ ሌላው ጉዳይ ለአሥራ ሁለት ሚሊየን ሰው የምግብ እርዳታ ባለፈው ዓመት እንዲደርስ ተደርጓል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ የ2 ነጥብ 8 ሚሊየን ሰው አስቸኳይ ድጋፍ መፈለግ ጉዳይ ግማሽ ታሪክ መሆኑን ከሚኒስትሩ ጋር ሆነው መግለጫ የሰጡት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ዩጂን ኦውሱ ተናግረዋል፡፡
ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ፡፡