በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እነአቶ አንዱዓለም አራጌ ጥፋተኛነት ተበየነባቸው


የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በእነ አቶ አንዱዓለም አራጌ ላይ ጥፋተኛ ናቸው ሲል ብይን ሰጠ።

አቶ አንዱዓለም አራጌ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ፍትህ ሲነፈጉ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ ገልፀው ባልፈፀምኩት ወንጀል የቅጣት ማቅለያ አልጠይቅም ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለቅጣት ውሣኔው ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህንኑ የዛሬውን ብይን ተቃውመው አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የጋዜጠኞች መብቶች ተሟጋቹ ሲፒጄ መግለጫ አውጥተዋል፡፡

ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል “ሃሣብን ለመግለፅ ነፃነት ጭለማ ቀን” ብሎታል ዕለቱን፡፡

በሽብር ፈጠራና መንግሥትን በኃይል የመጣል ሤራ የተጋነነ ክሥ ተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቀናቃኞች ጥፋተኝነት ተበየነባቸው” ይላል አምነስቲ፡፡

ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የፖለቲካው ተቃውሞ ግንባር ቀደም አባላት አንዱዓለም አራጌ እና ናትናዔል መኮንንም በሽብር ፈጠራ፣ የሽብር አድራጎትን በማበረታታት፣ መንግሥትን በኃይል በመጣል ሤራ እና ሌሎችም በርካታ ክሦች “ጥፋተኛ ናችሁ” ተባሉ ይላል አምነስቲ በመግለጫው፡፡

ባለፈው ጥር በአምስት ተከሣሾች ላይ የተላለፈውን ዓይነት ተመሣሣይ ብይን የተከተለው የዛሬው የጥፋተኝነት ብይን የተሰጠው በሌሎችም የተከሰሱ ጋዜጠኞችና አንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ላይ በሌሉበት ነው፡፡

“እኛ የምናምነው እስክንድር፣ አንዱዓለምና ናትናዔል የኅሊና እሥረኞች ናቸው ብለን ነው” ብለዋል የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ፈታሽ ክሌር ቤስተን፡፡

“የጥፋተኝነት ብይኑ የተላለፈባቸው - አሉ ቤስተን - በሕጋዊና በሰላማዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ምክንያት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በመንግሥት ላይ የሚደረገው ተቃውሞ ሰላማዊ እንዲሆን በመቀስቀሣቸው ነው” ብለዋል ቤስተን፡፡

“የዛሬው ዕለት ለፍትሕ በኢትዮጵያ ጨለማ ቀን ነው” ያሉት የአምነስቲዋ ክሌር ቤስተን ተከሣሾቹ ያለቅድመ ሁኔታና አሁኑኑ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እስከሞት ቅጣት የሚደርስ ፍርድ የያዘው የዚህ ክስ ሂደት “መንግሥት ተቃውሞን ለማፈን የያዘው ጥረት አካል ነው” ሲል ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ቡድን ሲፒጄ አስታውቋል፡፡

የሲፒጄ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠሪ ታም ሮድስ ለቪኦኤ ዛሬ በሰጠው መግለጫ “ይህ የሚያሣየው በምንም መንገድ የሚገለፅ ማንኛውንም ዓይነት ትችት ፈፅሞ የማይቀበልና በመገናኛ ብዙኃንም ላይ የማሳደድ ዘመቻ የሚካሂድን መንግሥት ነው” ብሏል፡፡

አብዛኞቹ ክሦች የተመሠረቱበት የኢትዮጵያው ፀረ-ሽብር ሕግ “ሃሣብን የመግለፅ ነፃነትን ከሃገሪቱ ጠራርጎ አስወጥቷል” ብሏል ሮድስ፡፡

በተመሣሣይ ሕግ ከመቶ በላይ የኦሮሞ የፖለቲካ ሰዎች ክሥ ተመሥርቶባቸው እየተሟገቱ ነው፡፡

አቃቢያነ ሕጉ ተከሣሾቹ “ሕገወጥ ከሆነው ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ሲንቀሣቀሱ የተገኙ ናቸው” ይላሉ፡፡

በዚሁ ክሥ ውስጥ የሁለት ዋነኛ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችና የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች ይገኙበታል፡፡

ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ፡፡

(ገፁ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ከማጫወቻዎቹ አንደኛውን ብቻ አስቀርተው የቀሩትን ያቁሟቸው፡፡)

XS
SM
MD
LG