በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ፀረ-ኤድስ እንቅስቃሴ ተመሠገነ


ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ኤችአይቪ/ኤድስን ለመቆጣጠር ያደረገችው እርምጃ ተመሠገነ፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታት ከዩናይትድ ስቴትስ ለዘርፉ የምታገኘው እርዳታ እንደሚጨምርም ተገልጿል፡፡

ይህ የተነገረው የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖምና በኢትዮጵያ የዩናይትድስ ስቴትስ አምባሣደር ዶናልድ ቡዝ ኢትዮጵያ የኤችአይቪ/ኤድስን ሥርጭት ለመመከት የሚያስችል የአምስት ዓመት የትብብር ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ነበር፡፡

አምባሣደሩ በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንዳሉት የሃገራቸው መንግሥት በዚህ የትብብር ስምምነት አማካይነት ለመደገፍ የፈለገው የኢትዮጵያ መንግሥት የኤችአይቪ/ኤድስን ወረርሽኝ ለመመከት ብቃትና ቀጣይነት ያለው ብሔራዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አመራር በመዘርጋቱ መሆኑን አመልክተው በኢትዮጵያ በኩል የተደረገውን እርምጃም በማመስገን ገልፀውታል፡፡

የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም በበኩላቸው በአፅንዖት የገለፁት ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ስቴትስ ያገኘችውን ድጋፍ የተጠቀመችበት “የጤና አገልግሎቱ ሥርዓት ውጤታማና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን በማድረግ ነው” ብለዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ለሦስት ዓመታት በግሎባል ፈንድ አማካይነት ከአራት መቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ በመለገሷ የአሜሪካን ሕዝብና መንግሥት አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ ገንዘብ ለፖለቲካ መጠቀሚያና ተቃዋሚዎችን ለመቅጣት ይጠቀምበታል በማለት በቅርቡ ሂዩማን ራይትስ ዋች የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ያወጣውን ዘገባ በተመለከተ ጋዜጠኞች ላቀረቡላቸው ጥያቄ አምባሣደር ቡዝ ሲመልሱ ሪፖርቱ በምር መወሰድ ያለበት እንደሆነ አምነው አሜሪካ ለጤሃው ዘርፍ የምትሰጠው የገንዘብ ድጋፍ በትክክለኛው መንገድ ጥቅም ላይ እንደሚውል በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም በበኩላቸው የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት የፈጠራ ክስ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት የኤድስ አጣዳፊ ድጋፍ ዕቅድ (ፔፕፋር) ባለፉት ስድስት ዓመታት ከአንድ ቢልዮን ተኩል በላይ ዶላር አግኝታለች፡፡ ለተጨማሪ ዝርዝር ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG