በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አፋር ክልል ውስጥ የተጠለፉትን አገር ጎብኚዎች ለማሰለቀቅ ጥረት ቀጥሏል


“ታጋቾቹን ለማስለቀቅ መንግሥት ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነው”

ባለፈው ሰኞ ሌሊት አፋር ኤርታአሌ አካባቢ በቱሪስቶች ላይ በደረሰው ጥቃት አምስቱ ሲገደሉ ሦስቱ ደግሞ ቆስለዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ዲፕሎማሲ ክፍል ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ “የተገደሉት ሰዎች አስከሬን ወደየአገሮቻቸው ተልኳል፤ የቆሰሉትም እየተመለሱ ነው” ብለዋል። በጥቃቱ ሁለት ጀርመናዊያንና አብረዋቸውም ሁለት ኢትዮጵያዊያን እንደታገቱ ይታወቃል።

እነዚህን ሰዎች ለማስለቀቅ የፀጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴ ሰለመኖሩ ተጠይቀው ቅድሚያ ዕድሉ የተሰጠው በኤርትራና በኢትዮጵያ ያሉት የአፋር ሽማግሌዎች ሰዎቹን ለማስቀቅ ለሚያደርጉት ጥረት ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ሌሎችም የፀጥታ ኃይሎች ግን ካሁን በፊትም እንደሚያደርጉት በአካባቢው መንቀሳቀሳቸውን እንደሚቀጥሉ ጨምረው ገልፀዋል።

የታገቱትን ለማስለቀቅ “መንግሥት ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነው፤ ሆኖም እንደአማራጭ በሠላማዊ መንገድ ማስለቀቅ የሚቻልበትን ሁኔታ ደግሞ ጊዜ ሰጥተን ልንንቀሳቀስበት የሚገባ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት “አደጋው የተጣለው በኤርትራ መንግሥት በተላኩ የታጠቁ ኃይሎች ነው” ሲል ይከስሳል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ግን በበኩሉ “ውንጀላው ተራ ቅጥፈትና ስም ማጥፋት ነው” ሲል አስተባብሏል።

ዝርዝሩን ከእስክንድር ፍሬው ዘገባ ያድምጡ።

XS
SM
MD
LG