በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"መንግሥት መቀሌን ተቆጣጥሯል" ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

"የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት መቀሌን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ማታ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባካሄደው ዘመቻ ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞቻችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ መቐለ ለመግባት ችሏል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማምሻውን ባወጡትና ለህዝቡ በኢትዮጵያ ቴሌቭዢን በተነበበው መግለጫቸው "የመከላከያ ሠራዊት በድል በገሠገሠባቸው የትግራይ አካባቢዎች ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለውን ክብር አሳይቷል" ብለዋል።

አስከትለውም "ጁንታው ካስታጠቃቸው ጥቂት የክፋት ኃይሎች ውጭ ያለው የትግራይ ሕዝብ መቐለ እስኪገባ ድረስ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሁሉ አድርጓል፤ ይህም የሠራዊቱን ድልና የጁንታውን ሽንፈት አፋጥኖታል" ብለዋል።

"ስግብግቡ ጁንታ በየትኛውም መመዘኛ ለትግራይ ሕዝብ አይመጥነውም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ሕዝብ ከእውነት ጋር በመቆምና የጁንታውን እኩይ ዓላማ በመፃረር ከቀበሌ ቀበሌ፣ ከዞን ዞን መቀሌ እስኪገባ ድረስ ተመሳሳይ ድጋፍ ለሠራዊቱ ሰጥቷል ብለው ለድጋፉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

"ጁንታው በሸሸበት ከተማና አካባቢ ሁሉ የጤና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ድልድዮችን፣ መንገዶችን፣ መሥሪያ ቤቶችን እያወደመ ሄዷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም የገዛ ወገኑ ጠላት መሆኑን አሳይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጁንታው እኔ ከሞትኩ ብሎ ያፈረሳቸውን መሠረተ ልማቶች በፍጥነት በመገንባት የትግራይ ሕዝብ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ ለማድረግ የቻልነውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ቀደም ብሎም የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይሎች ኤታ ማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ መከላከያ ሰራዊቱ መቀሌን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን በፌስ ቡክ ገጻቸው ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ከመንግሥቱ የመከላከያ ኀይሎች ጋር ላለፉት ሦስት ሳምንታት ሲዋጉ ከቆዩት የህወሃት ኀይሎች በኩል እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።

ውጊያው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የቴሌፎን እና የኢንተርኔት አገልግሎት ዝግ በመሆኑና ወደክልሉ ለመግባት በሚደረገው የበረታ ቁጥጥር የተነሳ ከሁለቱም ወገኖች በኩል የሚሰጡ መግለጫዎችን በነጻ ምንጭ ማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን ዜናው አክሎ ገልጿል።

ቀደም ብሎ ሮይተርስ ባወጣው ዘገባ የህወሃት መሪ ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በላኩለት የስልክ ላይ የጽሁፍ መልዕክት መቀሌ ላይ በከባድ መሣሪያ ድብደባ እየተካሂደ ነው ማለታቸውን አመልክቷል፥

የፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤ ኤፍ ፒም የረድዔት ሠራተኞች ይህንኑ እንዳረጋገጡ ዘግቦ ነበር ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጽሀፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም በበኩላቸው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የሲቪሎች አካባቢዎችን አይደበድብም፥ መንግሥት የመቀሌንም ሆነ የመላዋ ትግራይ ነዋሪ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት ቅድሚያ ትኩረቱ ማድረጉን ይቀጥላል" ማለታቸውን ሮይተርስ ጠቅሷል።

XS
SM
MD
LG