በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊ ክልል ኦብነግና የኢትዮጵያ መንግስት ሃይሎች ተጋጭተው ከ30 በላይ ተገደሉ


የኢትዮጵያ መንግስት 80 አማፂያን በአካባቢው ሚሊሻ ተገድለዋል ይላል

በሶማሊ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) በገላልሼና ባቢሌ ከተማ አካባቢ ባደረገው ጥቃት በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጉዳት ማድረሱንና እስረኞችን ማስፈታቱን አስታውቋል።

በገላልሼ በሚገኝ እስር ቤት በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ማስፈታቱን ኦብነግ ገልጾ፤ ከሳምንታት በፊት በኦጋዴን እርዳታ ያደርሱ የነበሩ የአለም የምግብ ድርጅት WFP ሰራተኞችንም በዚሁ ጥቃት ከኢትዮጵያ ሰራዊት ማስለቀቁን ድርጅቱ ገልጿል።

“በዚህ ውጊያ የወያኔ ወታደሮችም ተገድለዋል፤ የቀሩትም ከከተማው ወደ ባቢሌ ሸሽተዋል” ብለዋል የኦብነግ ቃል አቀባይ ሃሰን አብዱላሂ። ከተማውንም መቆጣጠራቸውን ነው አቶ ሃሰን የሚናገሩት።

የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ ሽመልስ ከማል ከታጣቂዎቹ ፍጹም የተለየ መግለጫ ሰጥተዋል።

“በገላልሼ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የታጣቂው ኦብነግ ሃይሎችን የአካባቢው ሚሊሻዎች የደፈጣ ጥቃት አድርሰው 80 ሸማቂዎች ገድለዋል። በክልሉ የፖሊስ ሃይሎች ላይ የደረሰው ጉዳት ሶስት ፖሊሶች ሲገደሉ፤ አራት ቆስለዋል” ብለዋል አቶ ሽመልስ ከማል።

ወደ ገላልሼ አካባቢ ደውለን ያገኘናቸው የአገር ሽማግሌዎች በጠቅላላው በግጭቱ 30 ሰዎች መሞታቸውን ነው የሚናገሩት።

በዚህ ግጭት ከሳምንታት በፊት ደብዛቸው ጠፍቶ የነበረው የአለም ምግብ ድርጅት WFP ሰራተኞች በኢትዮጵያ መንግስት ታስረው ማግኘታቸውንና አሁን በኦብነግ እጅ እንዳሉ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በክልሉ የእርዳታና የልማት ስራ የሚያከናውኑን ሰዎች ኦብነግ ጥቃት በማድረስ ይገድላል፣ የተቀሩትን አፍኖ ይወስዳል ሲል ይወነጅላል።

“በኦብነግ ሃይሎች የታገቱትን ሰዎች ፍለጋዉ ቀጥሎአል። እነዚህ ሰዎች የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት በከፈቱ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ሃይሎች እንደታገቱ ይታወሳል። “

በሶማሊ ክልል አንድ ሰራተኛው የተገደለበትና ሁለቱ ደግሞ የታገቱበት የአለም የምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ ጁቲት ሹለር የጠፉት ሰራተኞቹ እስካሁን እንዳልተገኙ ገልጸዋል። ጥቃቱን ተከትሎ የአለም የምግብ ድርጅት በአካባቢው እንቅስቃሴውን ገድቦ ነበር። አሁን የጸጥታ ሁኔታው ከተሻሻለ ድርጅቱ ለሶማሊ ህዝብ እርዳታ ማድረሱን ይቀጥላል ብለዋል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG