"ሜነሶታ ውስጥ ስብሰባ ከማድረጋችን በፊት የክልሉ አስተዳዳር በዚያ ወደሚገኙ የቤተሰቦቻቸው አባላት ሄደው ለልጆቻችሁ ደውላችሁ በስብሰባው እንዳይሳተፉ ንገሯቸው። ካልሆነ ግን እስር ቤት እንደምትገቡ፤ ቤትና ንብረታችሁን እንደምታጡ ንገሯቸው ብለው አስጠነቀቋቸው። እነርሱ ግን እሺ አላሉም። ከዚህ በፊት አድርጋችሁ ታውቁ የለ፤ የምታደርጉትን አድርጉ፤ አሏቸው። ከዚያም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጆች ሳይቀሩ ብዙ ሰዎች ታሰሩ።" በዩናይትድ ስቴትሷ የሜነሶታ ክፍለ ግዛት ነዋሪና የዱልሚ ዲድ ሊቀመንበር አቶ ዑመር ዶል
በቅርቡ በሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትና በጥቂት አጋሮቻቸው “ተፈጽመዋል” የተባሉ የመብት ጥሰቶችና በውጭ ሃገር የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች “እየደረሱብን” ነው ያሏቸውን የጥቃት ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት ደብዳቤ መነሻነት አንድ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።
ያን የቀደመ ዘገባ ተከትሎም በቅሬታው የተጠቀሱት በጊዜው እስር ላይ የነበሩ ግለሰቦች መለቀቃቸውን “ዱልሚ ዲድ” የተባለው ክሶቹን ያቀረበው ቡድን አባላት አስታውቀው ነበር።
ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ቡድኑ በሜነሶታ ክፍለ ግዛቶቹ መንትያ ከተሞች በሴንትፖል እና ሚኒያፖሊስ ባለፈው ወር መገባደጂያ ያካሄደውን የተቃውሞ ስብሰባ ተከትሎ፤ ዳግም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመው እስርና እንግልት ማገርሸቱን፤ በውጭ አገር በሚኖሩት የክልሉ ተወላጆች ላይ የሚቃጡት ማስፈራሪያና ዛቻዎችም መቀጠላቸውን አባላቱ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።
ክልላችንና ሕዝባችንን የሚመለከት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባደረግን ቁጥር በአገር ውስጥ በተለይ ዘመዶቻችን ላይ ማስፈራራትና ዛቻው እንደ አዲስ ይጀምራል።
አሁን አሁን ጫና እና ግፊቱ ቤተሰቦቻቸው በተቃውሞው ተሳትፈዋል ከተባሉ ወገኖች ጋር የሚዛመዱ ታዳጊ ሕጻናት አልቀሩም፤ ሲሉ ክልሉን ፕሬዚዳንት አብዲ መሃመድ ዑመርንና አጋሮቻቸውን የሚከሱት የዱልሚ ዲድ ሊቀመንበር አቶ ዑመር ዶል ናቸው።
በክልሉ አስተዳደር “እየተፈጸመ ነው” ያሉትን የመብት ጥሰት እና እንዲሁም ሙስና “በውል ያውቀዋል” ያሉት የዜጎችን መብት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት የፌድራል መንግስቱ ለምን በጉዳዩ ጣልቃ መግባትና ለምንስ “በሚሊዮኖች ላይ እየደረሰ ነው” ያሉትን በደል ማቆም እንዳልፈቀደ ይጠይቃሉ፤ አቶ ዑመር።
የዱልሚ ዲዱ ሊቀመንበር አክለውም፤ ይህን የቀደመ ጥያቄያቸውን ያዘለ ደብዳቤ ለመንግስት ማስገባታቸውን፤ እናም ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“እንዲህ ባለ ሁኔታ መቀጠል አይቻልም?” የሚሉት የቡድኑ ተጠሪ፤ የፌድራሉን ትኩረት ለማግኘት “አማራጭ ይሆናል” ያሉትን ይገልጻሉ።
አድማጮች ከሙስና እስከ ሕገ ወጥ እስርና ግድያ ቁጥሩ የበዛ ውንጀላ የቀረበባቸውን የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሞሃመድ ዑመርን ምላሽ ለማግኘት አሁንም እየተጠባበቅን ነው። በተጓዳኙ የክልሉን መንግስታዊ የሰብዓዊ መብት ኮምሽን አቶ ጀማል ዋርፋንም ለማግኘት ያደረግነው ጥረት እስካሁን ለጊዜው ባይሳካም፤ በጥረታችን የምንቀጥል እና እንደቀናን የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ መግለጽ እንወዳለን።
የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ