በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ተልእኮ የኢትዮጵያ ጦር ተሳትፎ ላይ ስምምነት ተደረሰ


በኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዋና ዲሬክተር ሬድዋን ሑሴንና በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራው የልኡካን ቡድን፣ ከሶማሊያው አቻቸው ጀነራል ኦዳዋ ዬሱፍ ራጌ እና አብዱላሂ መሐመድ ዓሊ ሳንባሎልሼ ጋራ ሞቃዲሾ
በኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዋና ዲሬክተር ሬድዋን ሑሴንና በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራው የልኡካን ቡድን፣ ከሶማሊያው አቻቸው ጀነራል ኦዳዋ ዬሱፍ ራጌ እና አብዱላሂ መሐመድ ዓሊ ሳንባሎልሼ ጋራ ሞቃዲሾ

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መንግሥታት፣ በዐዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልእኮ(አውሶም) ውስጥ፣ የኢትዮጵያን ጦር ተሳትፎ የሚያረጋግጥ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ የተደረሰው፣ በኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዋና ዲሬክተር ሬድዋን ሑሴንና በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራው የልኡካን ቡድን፣ ከሶማሊያው አቻቸው ጀነራል ኦዳዋ ዬሱፍ ራጌ እና አብዱላሂ መሐመድ ዓሊ ሳንባሎልሼ ጋራ፣ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ሞቃዲሾ ላይ ተገናኝቶ ከተነጋገረ በኋላ መኾኑን፣ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ብዙኀን መገናኛዎች ዘግበዋል።

የሶማሊያ ብሔራዊ የዜና አገልግሎት(ኤሶኤኔኤ) እንደዘገበው፣ የሁለቱ ልኡካን ውይይት፦ የሽብር ጥቃቶችን ለመግታት በሚካሔደው ዘመቻ፣ የቀጣናውን መረጋጋት በሚመለከቱ ጉዳዮች እና የኢትዮጵያ ኀይሎች በሶማሊያ በሚሰማራው የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ በሚኖራቸው ሚና ላይ ያተኮረ ነበር።

የዜና አገልግሎቱ ያስነበበው ባለዘጠኝ ነጥብ መግለጫ አክሎ፣ ሁለቱ ወገኖች፥ “በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መካከል የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ግንኙነቶች፣ ከሶማሊያ መንግሥት ጋራ ብቻ እንዲፈጸሙና የሶማሊያን ሕዝብ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ያከበሩ እንዲኾኑ ተስማምተዋል፤” ብሏል።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2012 አንሥቶ፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልእኮ(አትሚስ) አካል ኾና ቆይታለች። ኾኖም፣ ከሶማሊያ ከተገነጠለችው ራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋራ፣ በአውሮፓውያኑ ጥር 1 ቀን 2024 የተፈራረመችውን አወዛጋቢውን ስምምነት ተከትሎ፣ ሶማሊያ፥ “ሉዓላዊነቴንና የግዛት አንድነቴን የጣሰ ነው፤” ስትል ኢትዮጵያን ከወነጀለች በኋላ ግንኙነታቸው ሻክሮ መቆየቱ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ በበኩሏ፣ የሶማሊያን ሉዓላዊነት አልጣስኹም፤ ብትልም፣ ሶማሊያ ግን ከሶማሌላንድ ጋራ የተደረገው ስምምነት ካልተሻረ በቀር፣ በአገሯ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ጦር ለማስወጣት ዝታ ነበር።

ለአንድ ዓመት ያህል የዘለቀው ይኸው ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት፣ ሁለቱ ወገኖች እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ታኅሣሥ 11 ቀን፣ በቱርክ ሸምጋይነት፣ አንዳቸው የሌላቸውን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የማይጥሱ አካሔዶችን ለመከተል አንካራ ላይ በደረሱበት ስምምነት ተቋጭቷል።

በተጨማሪም፣ ለኢትዮጵያ አስተማማኝ እና ዘለቄታ ያለው የባሕር በርን ተጠቃሚነት የሚያስገኙና በሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ሉዓላዊ ሥልጣን ሥር የሚደረሱ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚፈጸሙ የሊዝ እና ሌሎች መሰል የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነቶች ላይ ለመወያየትም ተስማምተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG