በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሻምቡ ውስጥ በሁለት የትግራይ ተማሪዎች መገደል የተጠረጠሩ ተማሪዎች ተያዙ


ምሥራቅ ሃረርጌ ጨለንቆ
ምሥራቅ ሃረርጌ ጨለንቆ

ምሥራቅ ሃረርጌ ጨለንቆ ውስጥ በ15 ሰዎች ላይ የተፈፀመው ግድያ “የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ የተፈፀመባቸው ዘግናኝ እርምጃ ነው” ሲሉ የዞኑ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አማርረዋል።

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ግቢ የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ ሁለት ተማሪዎች ግድያ ጋር በተያያዘ ስድስት ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ከተንቤን - ትግራይ ወደ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሄደው በነበሩት አድኖም አሰግድ እና ሃጎስ (ለጊዜው የአባት ስም እያጣራን ነን) በሚባሉት የሆርቲከልቸር (የጓሮ ተክሎች ልማት) እና የገጠር ልማት የትምህርት ክፍሎች ተማሪዎች በነበሩት ወጣቶች ግድያ ውስጥ ‘እጃችሁ አለ’ ተብለው የተያዙት ተማሪዎች ኢብሣ ዳሆ፣ ብሮምሣ አበራ፣ ከማል በዳሣ፣ አሪቡ ከበደ እና አብዶ ካሣሁን የሚባሉና ስሙን እያጣራን ያለነው ሌላ ስድስተኛ ተጠርጣሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

የሻምቡው ግቢ መንስዔ አዲግራት ውስጥ መገደሉ የተገለፀ ተማሪ ጉዳይ መሆኑንም እማኞች ለቪኦኤ ጠቁመዋል።

ወደ ሻምቡ የመከላከያ ሠራዊትና ፌደራል ፖሊስ በመግባቱ ፍርሃት ያደረባቸው ተማሪዎች ዛሬ ወደ ግቢው አለመግባታቸውንና የአካባቢው ሰው እንዳስጠለላቸው አንድ እማኝ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በምሥራቅ ሃረርጌ ዞን ጨለንቆ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ሰርከማ በምትባል ቀበሌ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ኃይሎች ተኩስ ከፍተው አሕመዲን አሕመድ ሐሰን የሚባሉ ሰው ከተገደሉ በኋላ ከቀበሌዪቱ ወደ ጨለንቆ የሸሸው ሰውና የከተማዪቱ ነዋሪ ወደ አስተዳደሩ ለአቤቱታ እንደወጣ በዚያ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት ተኩስ ከፍተው ዘጠኝ ሰው መግደላቸው ተገልጿል።

ከዚያም ይኸው ኃይል ዲሼ በምትባል ቀበሌ ውስጥ ማሽላ በደቦ ለማንሣት ተሰብስበው በነበሩና ከጨለንቆው አጋጣሚ ጋር ግንኙነት ባልነበራቸው ገበሬዎች ላይ ተኩስ ከፍቶ ሌሎች ሰባት ሰዎችን መግደሉን የከተማዪቱ ነዋሪ ነኝ ያሉና ወደ አካባቢው ሄደው እንደነበር የተናገሩ እማኝ ለቪኦኤ ገልፀዋል።

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ፈዲላ ዳውድ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል “ወጣቱም ይሁን ሌሎቹ የተገደሉት የመብት ጥያቄ እያቀረቡ ሳሉ ነው፤ የተሰለፉትን ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ከማድረግ ይልቅ ጥያቄአቸውን በሰላማዊ መንገድ በማቅረባቸው ብቻ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ እርምጃ በተለይ ቀያቸው ውስጥ እርሻ ላይ በነበሩ ሰባት ገበሬዎች ላይ መተኮስና መግደል ያሣዝናል” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አምቦ ከተማ ውስጥ ከተማሪዎች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በክልሉ ፖሊስና በፌደራል ኃይሎች መካከል ግጭት መፈጠሩና ለአሥር ደቂቃ ያህል የተካሄደ የተኩስ ልውውጥ እንደነበረ ተገልጿል።

በግጭቱ ውስጥ ሕይወት ሳይጠፋ እንዳልረ የተነገረ ሲሆን አንዲት የዘጠኝ ዓመት ልጅም በጥይት ተመትታ ወደ ሆስፒታል መወሰዷ ተገልጿል።

ሰሜን ወሎ ውስጥም ውርጌሣ በሚባል ከተማ በተፈጠረ ግጭት አንድ ሰው ተገድሎ ሌላ ደግሞ መቁሰሉ ተሰምቷል።

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቪኦኤ እየጣረ ይገኛል።

የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ሻምቡ ውስጥ በሁለት የትግራይ ተማሪዎች መገደል የተጠረጠሩ ተማሪዎች ተያዙ
please wait

No media source currently available

0:00 0:13:27 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG