በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ የተመድን መርማሪ ቡድን ሥራ ለማስቆም የምታደርገውን ጥረት ማቋረጧን ሮይተርስ ዘገበ


 በጦርነቱ የተጎዳ ታንክ ሁመራ ከተማ አቅራቢያ እአአ 3/3/2021
በጦርነቱ የተጎዳ ታንክ ሁመራ ከተማ አቅራቢያ እአአ 3/3/2021

በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ጦርነት ወቅት የመብት ጥሰትና የጦር ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው የሚመረምረውን የመንግሥታቱ ድርጅት ቡድን ሥራ ለማስቆም ኢትዮጵያ ታደርግ የነበረውን ግፊት ማቆሟን ዲፕሎማቶችና ታዛቢዎች ነግረውኛል ሲል የሮይተርስ የዜና ወኪል ዛሬ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ም/ቤት ውስጥ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በማሰራጨት በተመድ የተቋቋመው ገለልተኛ መርማሪ ቡድን ሥራውን እንዲያቆም ስትጎተጉት እንደነበር ሮይተርስ ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ባለፈው ወር መዘገቡ ይታወቅል።

ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገውን ጦርነት የሚመረምረውና ብቸኛ የሆነው ዓለም አቀፍ መርማሪ ኮሚሽን በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች የጦር ወንጀልና ሌሎች ሰቆቃዎችን ለመፈጸማቸው “አሳማኝ ሁኔታዎች አሉ” በሚል ከሁለት ዓመት በፊት ሥራውን ጀምሯል።

መርማሪ ቡድኑ ባለፈው ጥቅምት የሰላም ሥምምነት ከተፈረመ በኋላም “ከባድ የመብት ጥሰቶች” ተፈጽመዋል በሚል ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ ጉባኤውን በማድረግ ላይ ያለውንና መሠረቱን በጀኒቫ ያደረገው የተመድ የሰብዊ መብቶች ም/ቤት የሚያደርጋቸውን ምርመራዎች ከዚህ በፊት አቋርጦ ባያውቅም፣ ኢትዮጵያ ም/ቤቱ እያካሄደ ያለውን ምርመራ 6 ወራት ቀደም ብሉ እንዲያቆም የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ባለፈው ወር አሰራጭታ ነበር።

አምስት ዲፕሎማቶችና የሰብዓዊ መብት ምንጭች ለሮይተርስ እንደነገሩት ግን ኢትዮጵያ ሃሳቧን እንድትተው ግፊት በመደረጉ የውሳኔ ሃሳቡን ከማቅረብ አፈግፍጋለች።

በጀኒቫ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ቡድን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አለመስጠቱን ሮይተርስ በሪፖርቱ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ግፊቱን ያቆመችው የመርማሪ ኮሚሽኑ የሥራ ግዜ እንደማይራዘም መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ መሆኑን ሁለቱ የሮይተርስ ምንጮች ተናግረዋል።

“በተደረሰው መግባባት መሠረት ምዕራባውያን አገሮች የውሳኔ ሃሳቧን እንድታቆም አድርገዋል፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የውሳኔ ሃሳብ ቢቀርብ ኖሮ የድምጽ ብልጫ ያገኝ ነበር” ሲሉ ዩኒቨርሳል ራይት ግሩፕ የተሰኘ የምርምር ተቋም ውስጥ የሚሠሩት ማርክ ሊመን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

“በምዕራባውያን ተጽእኖ የሚገፋ የሰብዓዊ መብት አጀንዳ ነው” በሚል የአፍሪካ አገራት በመቃወማቸው ምርመራው ፖለቲካዊ ድጋፉን እያጣ ነበር።

ኢትዮጵያ ቀድሞውንም ምርመራው ፖለቲካዊ ነው በሚል ተቃውሞ በማሰማት፣ ለመርማሪ ቡድኑ የሚመደበውን በጀት ለማስቆም ጥረት አድርጋለች። ምርመራውን በአገሬ ተቋማት አካሂዳለሁ ስትል ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።

XS
SM
MD
LG