በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዛሬ ዓመት... ኢትዮ ሳተላይት...


ኢትዮጵያ ሳተላይት የፊታችን መስከረም ውስጥ ልታመጥቅ ነው።

ለምርምርና ለልማት ጉዳዮች የታሰበችው ሳተላይት የንድፍ ሥራ ተጠናቅቆ ወደ ግንባታና ምርት ምዕራፍ መሸጋገሩን የኢትዮጵያ የኅዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰሎሞን በላይ ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።

በስምንት ሚሊዮን ዶላር ወጭ እየተገነባች ያለችውና ለውንጨፋ ስትደርስ ሰባ ኪሎግራም የምትመዝነው “ኢትዮሳት-ዋን” ምኅዋር ላይ የምታርፈው የፊታችን መስከረም 5/2012 ዓ.ም. እንደሆነ ታውቋል።

ውንጨፋው በተሣካ ሁኔታ ተከናውኖ ኢትዮሳት ዋን ሰማዩ ላይ ቦታዋን በያዘች በአራተኛው ቀን የመላ ኢትዮጵያን ሙሉ መረጃ፣ ከሃምሣ ቀናት ውስጥ ደግሞ የድፍን ዓለምን ሙሉ መረጃ እንጦጦ ለሚገኘው የመቆጣጠሪያና የክትትል ጣቢያ እንደምትመግብ ዶ/ር ሰሎሞን ተናግረዋል።

ከወጭው ሰባ አምስት ከመቶውን የሚሸፍነው በዓለምአቀፍ አጋርነትና ልገሣ የቻይና መንግሥት ሲሆን ሁለት ሚሊየን ዶላሩ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ እንደሆነ ተገልጿል።

ሙሉ በሙሉ ለሲቪል አገልግሎት ትውላለች የተባለችው የመጀመሪያዪቱ የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት የምትወነጨፈው ከቻይና ሲሆን የውንጨፋውን ክንዋኔ በቀጥታ ሥርጭት በመገናኛ ብዙኃን ለማስተላለፍ ኢንስቲትዩታቸው እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሰሎሞን በላይ አመልክተዋል።

ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀው ስያሜዋ እንዳለ ሆኖ በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ ስም ልትሰጧት አላሰባችሁም ነበር ወይ ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ሰሎሞን የመጀመሪያው ሃሣብ ኢትዮጵያን እንደአንድ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊያንንም እንደኢትዮያዊያን በአንድነት ማንፀባረቅና በዓለም ደረጃም እንደዚያው ማሳወቅ መሆኑን ጠቁመው ወደፊት ኢትዮጵያ የራሷን ሣተላይቶች እራሷ እያመረተች እራሷ ስታስወነጭፍ ሃገር በቀል ስሞችን እየሰጠች ልትልክ እንደምትችል ተናግረዋል።

ኢትዮሳት ዋን የኢትዮጵያን የገፀ-ምድርና የከርሰ-ምድር ሃብቶች ለማሰስ፣ ምርምር ለማድረግና ለማልማት ጉዳዮች፣ ለተፈጥሮዋ አካባቢ ጥበቃ፣ ለጤናና ለሌሎችም በርካታ አገልግሎቶች እንደምትውል ታውቋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የዛሬ ዓመት... ኢትዮ ሳተላይት...
please wait

No media source currently available

0:00 0:18:37 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG