በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ቴሌኮም በአአ የ5ጂ አገልግሎት ጀመረ


የኢትዮጵያ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ
የኢትዮጵያ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ

መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ቴሌኮም ከትናንት ሰኞ ጀምሮ የ5ጂ ሞባይል ስልክ አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ይህ ዝግ ሆኖ በቆየው ኢንደስትሪ ወደፊትም ይጀምራሉ ከተባሉት ዓለም አቀፍ ተፎካካሪዎች አስቀድሞ የተካሄደ ቁልፍ እምርጃ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ቀጣዩ ትውልድ የተባለው የ5ጂ አውታረ መረብ የሚያስተላልፈው የመረጃ ቋት 4ጂ ከተሰኘው ቢያንስ በ20 እጥፍ የሚፈጥን መሆኑ ተመልክቷል፡፡

እያበቡ ላሉ ቴክኖሎጂዎች፣ እንደ አሸከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎችም ሆነ ስማርት በተባሉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያቀላጥፍ ቁልፍ የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑም ተነግሮለታል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ አገልግሎቱ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ከመዳረሱ በፊት መጀመሪያ በአዲስ አበባ ላይ ሥራ ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎቱ መጀመር ይፋ በተደረገበት ወቅት “የ5ጂ አገልግሎት በተመረጡ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ተጀምሯል፡፡” ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ በሚቀጥሉት 12 ወራት አዲስ አበባ ውስጥና ከአዲስ አበባ ውጭ 150 በሚሆኑ አካባቢዎች አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ፍሬህይወት የአገልግሎት ዋጋው ምን ያህል እንደሚያስከፍል አልገለጹም፡፡

በአገሪቱ 64ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ኢትዮ ቴሌኮም በሌላ በኩል ባወጣው መግለጫ ለሚሰጠው አገልግሎት የቴክኖሎጂ መሳሪያዎቹን የሚያቀርበው የቻይናው ሁዋዌ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮም እኤአ እስከ ታህሳስ 31 ድረስ ባለው ግማሽ ዓመት ውስጥ 28 ቢሊዮን ብር ወይም 544.40 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስመዝገቡን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ቴሌኮምን 40 ከመቶ ድርሻ ለግል ባለሀብቶች ለመሸጥ ባለፈው ዓመት ሰኔ ጨረታ ማውጣቱ ተገልጿል፡፡ ባላፈው መጋቢት ወር መንግሥት ድርጅቱን በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዛወር ገብቶት የነበረውን ቃል፣ በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ባሉ የምጣኔ ሀብት ሁኔታዎች ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡

ባለፈው ታህሳስ በኢትዮጵያ ኢንደስትሪ ዘርፍ ተቆጣጣሪዎች የኮሚኒኬሽን ባለሥልጣን ለሁለተኛ የቴሌኮሙኒኬሽን ፈቃድ የወጣውን ጨረታ በመሰረዝ ወደፊት በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደገና የሚያካሂድ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ወደ 110 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ እኤአ ግንቦት 2021 ለሽያጭ ያቀረበችው ሁለት የሙሉ አገልግሎት ፈቃዶችን ብቻ መሆኑን በሮይተርስ ዘገባ ተገልጿል፡፡

የመጀመሪያውን ዙር ፈቃድ ያሸነፈው በኬንያው ሳፍሪኮም፣ ቮዳፎንና የጃፓኑ ሱሚቶሞ ኩባን ያዎች ጥምረት የሚመራው ድርጅት መሆኑ ተገልጿል፡፡ በማናቸውም ጊዜ አገልግሎቱን መስጠት እንደሚጀምር የተነገረ ሲሆን የአውታረ መረቦቹን የመዘርጋት ሂደት አስቀድሞ መጀመሩ ተነገሯል፡፡

የሚሰጡት ፈቃዶች በዓለም ላይ የቴሌኮም ገበያ ዝግ ከሆኑባቸው አንዷ በሆነችው አገር የምጣኔ ሀብቱን ነጻ ለማድረግ ለሚደረገው ግፊት እንደ ትልቅ እመርታ ተደርገው እንደሚወሰዱ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮም በአአ የ5ጂ አገልግሎት ጀመረ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:53 0:00

XS
SM
MD
LG