በዩናይትድ ስቴትስ ዩጂን - ኦሬገን ላይ እየተካሄደ ባለው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና ኢትዮጵያ በሴቶች ማራቶን 3ኛ የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋለች፡፡ አትሌት ጎተይቶም ውድድሩን የሻምፒዮን ሺፑ ክብረወሰን በሆነ 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች፡፡
በኢትዮጵያውያን እና በኬንያውያን አትሌቶች መካከል ብርቱ ፉክክር በተካሄደበት በዚህ ውድድር፣ ጎተይቶም ገብረስላሴ እና ኬንያዊቷ ጄፕቱም ኮሪር የመጨረሻዎቹን በርካታ ኪሎሜትሮች ብቻቸውን ተፋልመዋል፡፡ ሆኖም፣ የቶኪዮ ማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ጎተይቶም፣ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሁለት ኪሎሜትሮች ሲቀሩት ፍጥነቷን ጨምራ ወደፊት በመውጣት የድሉ ባለቤት ሆናለች፡፡
በዘጠኝ ሰከንድ ዘግይታ የገባችው ኮሪር ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያውን ስታሸንፍ፣ ትውልደ ኬንያዊቷ የእስራኤል አትሌት ቼምታይ ሳልፒተር 3ኛ ሆና አጠናቃለች፡፡ የዛሬውን ውጤት ተከትሎ፣ እስካሁን 3 የወርቅ እና 1 የብር ሜዳሊያ፣ በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት፣ ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ስቴትስ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ቅዳሜ ዕለት በተካሔደው በሴቶች 10 ሺ ሜትር ውድድር ያሸነፈች ሲሆን፣ በውድድሩ የተሰለፈችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘች አትሌት ነች፡፡
በኢትዮጵያውያን፣ በኬንያዊያንና በትውልደ ኢትዮጵያዪቱ ኔዘርላንዳዊት አትሌት ሲፋን ሀሰን መካከል ብርቱ ትንቅንቅ በታየበት በዚህ ውድድር የአምስት ሺህ ሜትርና የአሥር ሺህ ሜትር ርቀቶች የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቷ ለተሰንበት ኬኒያዊያን ተፎካካሪዎቿን ቀድማ ድል ተጎናፅፋለች።
እሁድ እለት በተካሔደው የወንዶች ማራቶን ደግሞታ ምራት ቶላ እና ሞስነት ገረመው የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ውድድሩ ሊጠናቀቅ 10 ኪሎሜትሮች ሲቀሩት ጀምሮ ከተፎካካሪዎች ተነጥሎ ወደፊት የገሰገሰው ታምራት ቶላ፣ የ42 ኪሎሜትሩን ርቀት ለመጨረስ በ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ የፈጀበት ሲሆን ይህ ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና የማራቶን ክብረወሰን ሆኗል።