· በኪነ ጥበብ ሥራዎች እና ባለሞያዎች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ ሌላ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ጥሪ አቀረበ
ባለፉት ዓመታት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ተጽእኖዎች እንደተደረጉበት በሳምንቱ መጨረሻ በለቀቀው መግለጫ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ)፣ ደርሰውብኛል ያላቸውን ጥቃቶች እና ጫናዎች አትቷል።
አመራሮቹ እና ሠራተኞቹ፣ በመንግሥት ኀይሎች ክትትል፣ ዛቻ እና እስር እንደሚፈጸምባቸው፣ የመብቶች ተሟጋች ድርጅቱ በመግለጫው አመልክቷል።
“መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሰዓት 10፡30 አካባቢ፣ ሲቪል የለበሱ ሁለት የመንግሥት የደኅንነት አባላት፣ ወደ ኢሰመጉ የሥራ ኃላፊ መኖሪያ ቤት በመሔድ፣ ዛቻ እና ማስፈራራት ፈጽመዋል፡፡ እነዚኽ የደኅንነት አባላት፥ አመራሮቹ የሚሠሩትን ሥራ እንደሚያውቁ፣ እየተከታተሏቸው እንደኾነ፣ የሰብአዊ መብቶችን ከማስከበር ሥራቸው እንዲቆጠቡና መንግሥትን በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ከመወንጀል እንዲቆጠቡ፣ ካልኾነ ግን ዋጋ እንደሚከፍሉ” ማስጠንቀቃቸው፣ በቅርብ ጊዜያት የተፈጸሙ ናቸው ካላቸው ዝርዝር ውስጥ ይገኝበታል።
ከዚኽም ቀደም ተመሳሳይ ድርጊት፣ በኢሰመጉ የሥራ ኃላፊ ላይ መፈጸሙን ድርጅቱ አውስቷል።
በተለያዩ ክልሎችም በሠራተኞቹ እና በአባላቱ ላይ ወከባ፣ ጥቃት እና ዘረፋ እንደሚፈጸም፣ ይህም በአብዛኛው የመብቶች ጥሰትን ለማጣራትና መረጃ ለመሰብሰብ በሚደረግ ጥረት ወቅት የሚያጋጥም መኾኑን ኢሰመጉ አስረድቷል።
በሌላ በኩል፣ “በኪነ ጥበብ ባለሞያዎች እና ሥራዎች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ” ሲል፣ የኢትዮጰያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ጥሪ አድርጓል።
ኪነ ጥበብን ማፈን የሐሳብ ነጻነትን መጋፋት ስለኾነ፣ ተገቢ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፤”
“ኪነ ጥበብን ማፈን የሐሳብ ነጻነትን መጋፋት ስለኾነ፣ ተገቢ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፤” ሲሉ፣ የማዕከሉ ዋና ዲሬክተር አቶ ያሬድ ኀይለ ማርያም ጥሪ ማድረጋቸውን መግለጫው አመልክቷል።
ማዕከሉ በዚኹ መግለጫው፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በኪነ ጥበብ ባለሞያዎች እና የጥበብ ሥራዎች ወይም የኪነ ጥበብ መድረኮች ላይ እየደረሱ ያሉ ወከባዎች፣ ክልከላዎች፣ እስሮች እና ጫናዎች፣ ከዕለት ዕለት እየበረቱ መምጣታቸው ድርጅታችንን ያሳስበዋል፤” ብሏል።
“ቧለቲካ” የተባለ ቴአትር፣ መድረክ መከልከሉን እንዲሁም “እብደት በኅብረት” የተሰኘው የመድረክ ተውኔት አዘጋጅ እና ተዋናይ ባለሞያዎች እንደታሰሩ ማረጋገጡን ማዕከሉ አስታውቋል።
በመጨረሻም ማዕከሉ ባስተላለፈው ጥሪ፣ መንግሥት፥ ለጥበብ ባለሞያዎች የኪነ ጥበብ ምኅዳሩን እንዲያሰፋና ያሰራቸውንም ባለሞያዎች እንዲለቅ ጠይቋል። ድርጅቶቹ ባወጡት መግለጫ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ምላሽ እንዳገኘን ይዘን እንመለሳለን።
መድረክ / ፎረም