በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአሁኑ የክረምት ወቅት አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ክልሎች ዝናብ ያገኛሉ


በአሁኑ የክረምት ወቅት በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲኦሮሎጂ አገልግሎት ኤጀንሲ ተጠባባቂ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዱላ ሻንቆ አስታወቁ፡፡

ዳይሬክተሩ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ በሰጡት ማብራሪያ ኤጀንሲያቸው ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የየአራት ወሩን የአየር ሁኔታ የሚናገር የወቅት ትንበያ እንደሚያወጣ አመልክተው አሁን ባለንበት የክረምት ወራትም ከሰኔ እስከ መስከረም በሚቆየው የክረምት ወቅት የሚጥለው ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ የመጣ፣ በጊዜው የገባና በጊዜው የሚወጣ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት ምዕራብ ትግራይ፣ ምዕራብና መካከለኛው አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ፤ ጋምቤላ፣ ምዕራብ፣ መካከለኛና ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ ሐረሪ፣ ድሬዳዋ፣ ሰሜን ሶማሌ፣ ደቡብ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መደበኛና ከመደበኛ በላይ፤ ምሥራቅ ትግራይ፣ ምሥራቅ አማራና አፋር በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ዝናብ የማግኘት ዕድል እንዳላቸው፤ በአንዳንድ ኪስ ባሏቸው አካባቢዎች ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አቶ ዱላ ሻንቆ አመልክተዋል፡፡ በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ቆላማና የጠረፍ አካባቢዎች መደበኛው ደረቅ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር ገልፀዋል፡፡

ገበሬውን ጨምሮ በኢኮኖሚው ውስጥ ስፋት ያላቸው ተጠቃሚዎች ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሚሰጣቸውን ትንበያና መረጃ በመገናኛ ብዙኃንና በቀጥታም ከመሥሪያ ቤቱ እያገኙ እንደሚከታተሉና ሥራ ላይ እንደሚያውሉትም አቶ ዱላ አመልክተዋል፡፡

እንደጎርፍ፣ ድርቅ፣ ንፋስ፣ በከባቢ አየር ውስጥ ያሉ ደቃቃ አካላትና አቧራን የመሣሰሉ የአደጋ ሁኔታዎችንም ኤጀንሲያቸው እየተከታተለ እንደሚጠቁም፣ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶችም ውስጥ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት አባል ሆኖ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በየአይሮፕላን ጣቢያው ላይ ኤጀንሲያቸው ክፍል እንዳለው ጠቁመው ማንኛውም አይሮፕላን የሚቲኦሮሎጂ መረጃ በቅድሚያ ሣይይዝ እንደማይነሣ ገልፀዋል፡፡

በዚህ ዓመት ይደርሣሉ ብለው የሚያስቧቸው ወይም የተተነበዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ይኖሩ እንደሆነም አቶ ዱላ ተጠይቀው ድርቅም ይሁን ጎርፍ ወይም ያለጊዜው የሚጥል ዝናብ ይኖራል ወይም ዝናቡ ያለጊዜው ይቋረጣል የሚል ትንበያ እንደሌላቸው አመልክተዋል፡፡ ለማንኛውም ግን በወንዞችና በሜዳማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ምንጊዜም ሊደርስ ከሚችል ድንገተኛ መጥለቅለቅ እራሣቸውን ነቅተው መጠበቅ መደበኛ የኑሯቸው ሁኔታ አካል እንዲሆን አሣስበዋል፡፡

በዓለም ዙሪያ የሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ላይ እንዴት እንደሚንፀባረቅ የተጠየቁት የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲው ኃላፊ ሲመልሱ "በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ስምምነት ማዕቀፍ (UNFCCC) አለ፤ በዚያ ማዕቀፍ በሠፈሩ መለኪያዎች ወይም ማሣያዎች መነሻነት በተደረጉት ጥናቶች የኢትዮጵያ የሙቀት መጠንና የዝናብም መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ ይታያል፤ ይሁን እንጂ ጥናቱ በቂ አይደለም፤ ወደፊትም የሚጠኑ ነገሮች አሉ" ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG