በሀገር ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ጥሩ ግንኙነት አለ ማለት አይቻልም። ለዚህ ማሳያው፥ በሀገርአቀፉ ምርጫ ከኢሕአዴግ ቀጥሎ ያሉትን ሦስት ቦታዎች በመያዝ ባጠናቀቁት ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለው ሁኔታ ነው። መድረክ፥ ኢዴፓና መኢአድ በምርጫው አካሄድና ውጤት ላይ ያላቸው አስተያየት ተመሳሳይ ቢሆንም፥ ቅሬታቸውን እንኳ አንድ ላይ አላስተባበሩም። የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የምርጫ ቅስቀሳም በነዚህ ልዩነቶቻቸው ላይ ያተኰረ ነበር። «ተቃዋሚዎች እርስ በርሣቸው እንኳ አይስማሙም በሚል»
ከልባቸው ይሁን አይሁን ባይታወቅም፥ እነዚህ ተቃዋሚዎች ስለ መተባበር ማንሳት የጀመሩት፥ የምርጫው ውጤት ከተገለጸ በኋላ ነው።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ትላንት በሰጠው መግለጫ፥ እንደየ ሁኔታው እስከ ውህደት በሚደርስ ትስስር ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አቶ ማሙሸት አማረ እንዳብራሩት፥ አንደኛ ህብረብሄራዊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያካተተና፥ ህብረ ብሄራዊ ያልሆኑት ድርጅቶች ደግሞ፥ በቀጥታ ወደ ውህደት እየመጡ በጋራ መሥራትን እንፈልጋለን ብለዋል። በኢትዮጵያ አብሮ መሥራት እስካልተቻለ ጊዜ ድረስ፥ ተበታትኖ መቀጠሉ ለሀገሪቱም ሆነ ለሕዝቡ አስቸጋሪ ይሆናል ሲሉም አስረድተዋል። አሁን ያለው መንግሥትም ጉልበት አግኝቶ እንደፈለገው በየቦታው እያንዳንዳችንን በተናጠል እየነጠቀ ወደ ሥልጣን የሚወጣው በጋራ ቆመው ለሕዝብና ለዓላማቸው በጽናት ያለመቆማቸው ነው ሲሉም አክለዋል።
ትላንት መኢአድ በሰጠው መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች በተጨማሪ፥ የሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች የጋበዘ ቢሆንም አብዛኞቹ አልተገኙም። በጋራ ለመሥራት ማናቸውንም እርምጃ እንደሚወስድ የገለጸው መኢአድ ግን ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።