በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎችን የግብፅ ነጭ ለባሾች ሲሉ ከሰሱ


ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትናንት ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጡ።


ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትናንት ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት በኢትዮጵያ አመፅ ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው፥ ድርጊቱ አባላቱን ዋጋ ያስከፍላቸዋል ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወቃል።

አንድነት ይህን ከባድ ክስ እንዴት ያየዋል?

የፓርቲውን የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስዬ አብርሃን አነጋግረናል። ሰሎሞን ክፍሌ ነው ለምሽቱ ዓብይ ርዕስ ያወያያቸው።

ከታሰሩት የመድረክ አባላት አብዛኞቹ የኦነግ አባላት ሽብርና አመፅ ለማቀናጀት ሲንቀሳቀሱ ማስረጃ የተገኘባቸው መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። አቶ መለስ በመድረክ በተለይም አባሉ በሆነው በአንድነት ፓርቲ ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንቱ የፓርላማ ንግግራቸው ላይ «ተቃውሞና ሽብር ለመቀስቀስ እየተቀፈቀፈ ነው ያሉት ሤራ» ምን ሊያስከትል እንደሚችል በዝርዝር አላብራሩም። Facebook በሚባለው ማህበራዊ መረጃ መለዋወጪያ መረብ ዌብሳይት የተያዘው ዘመቻ ግን የአቶ መለስ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ግንባር ሥልጣን የያዘበት 20ኛ ዓመት በመጪው ወር ሲከበር ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ እንዲደረግ ጥሪ ያቀርባል።

አቶ መለስ በትላንትናው የፓርላማ ንግግራቸው ላይ ተቃዋሚዎችን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ አለመረጋጋት ለመፍጠር ይሞክራሉ ያሏቸውን ሁለት ያካባቢውን ሀገሮችም ከሰዋል። የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርን ትረዳለች ያሏትን ኤርትራን እርሣቸውም ፕሬዘዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን ለመገልበጥ የሚታገሉትን አማጽያን በማገዝ እንደሚበቀሉ አስገንዝበዋል።

በአባይ ወንዝ ላይ ግዙፍ ግድብ ለማነጽ የተያዘውን ጥረት በገንዘብ እንዳይታገዝ ለማገድ ግብፅ ይዛለች ያሉት ዘመቻ እንደማያስፈራቸው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተው፥ ግብጽ ብትተናኰልና፥ አንድም ዓለምአቀፍ ለጋሽ አገር ገንዘብ ለመስጠት ባይስማማም፥ 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር የሚያስወጣው የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮዤ ሥራ ይቀጥላል ሲሉ አስታውቀዋል።

ዘገባውን ያዳምጡ

XS
SM
MD
LG