የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የተባሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታቸውን በተመለከተ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ይግባኞቻቸውን ትላንት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ለማስገባት ሞክረው ነበር። ይሁንና የይግባኝ አቤቱታው ለፍርድ ቤቱ የደረሰው በህግ ከተቆረጠለት የቀን ገደብ አልፎ ስለነበር ጥያቄያቸው እንደማይስተናገድ ተገልፆላቸው ነበር።
እንደገና የማስፈቀጃ ጥያቄ አቅርበውም አስቀድሞ የተደረሰው ውሳኔ ትክክል እንዳልሆነና የይግባኝ አቤቱታው ለፍርድ ቤቱ ገቢ የተደረገው ህጉ በደነገገው በአምሥት ቀን ገደብ ውስጥ በመሆኑ ሁለቱም የፖለቲካ ድርጅቶች የይግባኝ ማመልከቻዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ተፈቅዶላቸዋል።
ፍርድ ቤቱ የይግባኝ አቤቱታትውን ተመልክቶ የሚከተለውን ብይን ወይንም ትእዛዝ በቅርብ ግዜ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።