በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የማሌዥያው ኩባንያ የነዳጅ ፍለጋውን ለኢትዮጵያ ኩባንያ አስረክቦ ከሀገር ሊወጣ ነው


ላለፉት ሰባት አመታት በኢትዮጵያ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ላይ የቆየው የማሌዢያ ኩባንያ ፔትሮናስ በኢትዮጵያ ስራውን አቁሞ ከሀገር እየወጣ ነው።

የነዳጅ ኩባንያው በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል በተለይ በኦጋዴን አካባቢ ለሰባት አመታት ያህል ነዳጅ ሲፈልግ ቆይቷል።

በክረምቱ ወራት ፔትሮናስ ለሰራተኞቹ የስንብት ደብዳቤ ከሰጠ በኋላ ድርጅቱ ኢትዮጵያን ለቆ እንደሚወጣ ግልጽ እየሆነ ቢመጣም፤ በይፋ ድርጅቱ እስካሁን መግለጫ አልሰጠም ነበር።

በአዲስ አበባ ፔትሮናስ የዝግ ስብሰባ አድርጎ፤ ስራው መጠናቀቁንና ሳውዝ ዌስት ኤነርጂ ለተባለ ኢትዮጵያዊ ኩባንያ የነዳጅ ፍለጋ ያከናውንባቸው በነበሩት ስፍራዎችና ቁሳቁሶች ተረክቦ ስራ እንዲጀምር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል።

የ South West Energy ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ አሸናፊ ለካፒታል ጋዜጣ ሲናገሩ “ይሄ ለ South West Energy ትልቅ እድል ነው። የነዳጅ ፍለጋና ምርቱን ለማስፋፋት ያስችለዋል” ብለዋል።

ሳውዝ ዌስት ኤነርጂ በኢትዮጵያ በነዳጅ ዘይት ፍለጋ ከተሰማሩ ጥቂት አገር በቀል ድርጅቶች አንዱ ነው። ድርጅቱ ከፔትሮናስ ጋር የደረሰውን ስምምነት አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

ፔትሮናስ በኢትዮጵያ እስካሁን ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዳወጣ የሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል። የካሉብና ሂላላ መሬቶች ላይ ፍለጋ ለማድረግ ለቀድሞው ማእድንና ኤነርጂ ሚኒስትር ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከፍሏል ይላል ዘገባው።

ይሄንን ያህል ገንዘብ የወጣበትን ስራ ለምን እንዳቆመ ፔትሮናስ በግልጽ የተናገረው የለም። ሪፖርተር ጋዜጣ የፔትሮናስ የነዳጅ ፍለጋ ባለሙያዎችን ጠቅሶ “በኦጋዴንና በገናሌ አካባቢ በቆፈሩት የፍለጋ ጉድጓድ የጋዝ ፍሰት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ይሁንና የጋዝ ፍሰቱ መጠነኛ እንደሆነ ተናግረዋል” ሲል ዘግቧል።

የሳውዝ ዌስት ኢነርጂ ስራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ አሸናፊን ለማነጋገር ፈልገን በጉዳዩ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

ከዘገባዎች እንደተረዳንው ድርጅቱ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለነዳጅ ማውጫ መድቦ ይንቀሳቀሳል።

በኦጋዴን አካባቢ የነዳጅ ማውጣት ስራ እግጅ አስቸጋሪ በሆነ የአየር ጸባይና የጸጥታ ሁኔታ የሚከናወን ነው። ከአምስት አመታት በፊት ቻይናዊያንና ኢትዮጵያዊያን በስራቸው ላይ ሳሉ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ታጣቂዎች ጥቃት አድርሰው በርካታ ሰዎችን ገድለዋል።

ፔትሮናስም ሆነ ሌሎች የነዳጅ ዘይት አውጭ ድርጅቶች በአካባቢው እንዳይንቀሳቀሱና ፍለጋ እንዳያከናውኑ የሚጠይቀው ኦብነግ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ሳውዝ ዌስት ኤነርጂ የህወሃት የንግድ ድርጅት ነው፤ በአካባቢው የሚገኘውን ሀብት ከኦጋዴን ህዝቦች ለመውሰድ የሚጥሩ ሃይሎችን በሙሉ እንቃወማለን ብሏል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG