በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዴቪድ ሺን ስለ ኦጋዴን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ኦብነግ


አምባሳደር ዴቪድ ሽን
አምባሳደር ዴቪድ ሽን

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) በሶማሌ ክልል ማዕከላዊቱ ደገሕቡር አካባቢና በስተደቡብ ባለችው ቀብሪደሃር በሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃቶችን ማድረሱን በቅርቡ አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የተባበረው የምዕራብ ሶማሌ ነፃነት ግንባር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት መፈረሙና ንግግሮቹ አሁንም እንደቀጠሉ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ተከታይ ውይይታቸውን ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

በአንድ በኩል የሰላም ድርድርና ስምምነት ከኦጋዴን አካባቢ ሲሰማ በሌላ በኩል ደግሞ የጥቃትና የግጭት ዜናም እየወጣ ነው፡፡

ስለመጠነ ሰፊው የኦብነግ ጥቃት የተናገሩት ለንደን የሚገኙት የኦብነግ የውጭ ግንኙነቶች ፀሐፊ አብዲራህማን ማኅዲ ሲሆኑ መግለጫው መሠረት የሌለው ነው ሲል ደግሞ አንድ ለጊዜው ማንነቴ አይገለፅ ያለ ለኢትዮጵያ መንግሥት ቅርበት ያለው ምንጭ አመልክቷል፡፡

ምንጩ የኦብነግን አብዛኛውን አመራርና ሠራዊቱን የሚወክሉ ቡድኖች ከመንግሥት ጋር የዕርቅና የሠላም ድርድር ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ አክሎም ኦብነግ በአሁኑ ሰዓት በማንም ላይ ጥቃት ማድረስ በሚችልበት ሁኔታ ላይ የሚገኝ ኃይል አለመሆኑን አመልክቶ "አንዳንድ በሕገወጥ እንቅስቃሴ ለመቀጠል የወሰኑ ሦስት እና አራት እየሆኑ በተበታተነ ሁኔታ የሽብር ተግባር የሚፈፅሙ የጉዳትና የውድመት ዜና በማውጣት በመገናኛ ብዙኃኑ ትኩረት ውስጥ ለመቆየት ያልያዙትን ያዝን፣ ያልማረኩትን ማረክን ከሚሉ በስተቀር አድርሰናል የሚሉት ጥቃትም ሆነ ጉዳት ውሸት ነው" ብሏል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካን በተለይም ደግሞ ይህንን የኢትዮጵያ ሶማሌ የፖለቲካ ጉዳይ በቅርብ ከሚከታተሉ ምሁራንና ዲፕሎማቶች ዴቪድ ሺን አንዱ ናቸው፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የዓለምአቀፍ ጉዳዮች መምህርና ቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሣደር ሚስተር ዴቪድ ሺን ስለእነዚህ መግለጫዎችና በአሁኑ ወቅትም በአካባቢው ስላለው ሁኔታ አጠር ያለ ግምገማ ለአሜሪካ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

ሚስተር ሺን በዚሁ ግምገማቸው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትና የተባበረው የምዕራብ ሶማሌ ነፃነት ግንባር የሰላም ስምምነት መፈረማቸውና እርሣቸው በወቅቱ በአጋጣሚ አዲስ አበባ ውስጥ ስለነበሩ ከፊርማው ሥነ-ሥርዓት በኋላ ከግንባሩ መሪ ሼኽ መሐመድ ሁሴን ጋር መነጋገራቸውን አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በአጠቃላይ "ሰላም አለ ወይም የለም" ለማለት አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው የሚናገሩት አምባሣደር ሺን ሁኔታው በሰፊው የኦጋዴን ክልል ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ዛሬ የተሻለ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

ኦብነግ ሰሞኑን አድርሻቸዋለሁ የሚላቸውን ጥቃቶች እውነትነትና ሃሰትነት ለማረጋገጥ እንደሚከብዳቸው የሚናገሩት አምባሣደር ሺን ምን ያህል ክብደት ያለውና ለምን ያህል ጊዜ የተራዘመ ውጊያ ማካሄድ ይችላል የሚል ጥያቄ ካልተነሣ በስተቀር በተለይ በሞሐመድ ዑማር ኦስማን የሚመራው ቡድን ጥቃት የመሠንዘር አቅም አሁንም እንዳለውና ብዙውን ጊዜም አደጋ ስለመጣሉ የሚናገረው እርሱው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ስለመሰል ጥቃቶች መግለጫ በሚሰጡበት ጊዜ የኦጋዴኖቹ አማፂያንም ሆኑ መንግሥት የማጋነን አዝማሚያ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ እነዚህ የኦጋዴን አማፂያን ከኤርትራ የተወሰነ ድጋፍ እንደሚያገኙም ዴቪድ ሺን ጠቁመዋል፡፡

አምባሣደሩ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚታየውን "ተገቢነት ያለው" የሚሉት ቅሬታ አስመልክቶ ሲናገሩም በዚያ ይበልጥ ልማት፣ ይበልጥ ዴሞክራሲና እስከ ታች የወረደ የሥልጣን ክፍፍል መኖር እንዳለበት ገልፀው የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር አንጃዎች የሚያራምዱትን የመገንጠል ሃሣብ እንደማይደግፉና ብልህነት ነው ብለውም እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG