በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በትግራይ ያለው የኢንተርኔት እገዳ የሚነሳበት ቁርጥ ያለ ቀን የለውም” የቴክኖሎጂ ሚኒስትር


ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ
ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ

በትግራይ የኢንተርኔት አገልግሎት መልሶ የሚጀምርበት “የጊዜ ሰሌዳ የለውም” ሲሉ አንድ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣን ተናገሩ።

በትግራይ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚጀምረው የስልክ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲቀጠል ጎን ለጎን መሆኑን እና ሥራውን በተመለከተ ግን ቁርጥ ያለ የጊዜ ሰሌዳአለመኖሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ ትናንት ማክሰኞ ተናግረዋል ሲል አሶስዬትድ ፕረስ ዘግቧል።

በጥቅምት 2013 በፌዴራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ጦርነቱ ከጀመረ ጊዜአንስቶ ከ5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖርባት የትግራይ ክልል በአብዛኛው ከኢንተርኔት ስልክና ባንክ አገልግሎት ውጪ ሆኗለች።

የረድኤትድርጅቶችና የስብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች እንደሚሉት የግንኙነት መሥመር እገዳ መጣሉ ዕርዳታ የማድረስ ሥራን እንደጎዳና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እንዳባባሰ ይናገራሉ ሲል አሶስዬትድ ፕረስ ዘግቧል።

ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ላይ “የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎትን ለይቶ መቀጠል ብቻ ሳይሆን ሁሉም አገልግሎቶች የሚቀጥሉበትን አጠቃላይ ሥራ ነው እያቀደ ያለው፣ ምክንያቱም እንደ ሕዝብ፣ እንደ መንግሥት የሚያስግፈልገን ያ ነው” ማለታቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ሚኒስትሩ “የጊዜ ሰሌዳ ግን የለንም” ብለው መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ከአንድ ወር በፊት የተደረሰው የሰላም ሥምምነት መንግሥት መሠረታዊ አገልግሎቶችን በትግራይ እንዲያስቀጥል የሚያዝ ቢሆንም እስከ አሁን እገዳው አልተነሳም ሲል ሪፖርቱ ጠቁሟል።

ባለፈው ነሐሴ ጦርነቱ እንደና ሲያገረሽ፣ የዕርዳታ ሥራዎች ተስተጓጉለው የበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ወደ ክልልሉ ዕርዳታ እየገባ እንደሚገኝ፣ ነገር ግን ወደ አንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች መድረስ አሁንም አስቸጋሪ እንደሆነበት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መግለጹን ሪፖርቱጠቁሟል።

በትግራይ ላይ የኢንተርኔት እገዳው ባለበት ባሁኑ ሰዓት ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄዱ ነቀፌታን እንዳስከተለ ሪፖርቱ አውስቷል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ 22 ጊዜ ኢንተርኔት መዝጋቷን ‘አክሰስ ናው’ የተሰኘው የኢንትርኔት መብት ቡድን መግለጹንና፣ በትግራይ ላይ ያለው እገዳ “በዓለም ረጅሙ እገዳ” እንደሆነ የቡድኑ ሥራ አስፈጻሚ ብረት ሰሎሞን መግለጻቸውን የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

የግንኙነት መሥመር እገዳ መጣሉ ዕርዳታ የማድረስ ሥራን እንደጎዳና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እንዳባባሰ፤ እንዲሁም በታጣቂዎች ዘንድ በሕግ ያለመጠየቅን ስሜት እንደፈጠረ የረድኤት ድርጅቶችና የስብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ይገልጻሉ ብሏል ሪፖርቱ።

የተመድ መርማሪዎች ሁለቱንም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች በመብት ጥሰት፣ ግድያ፣ ስቃይ እና አስገድዶ መድፈር መወንጀላቸውን ሪፖርቱ አስታውሷል።

“ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከታጠቁ አማጺያን ጋር በተጋፈጠችበት ወቅት፣ የኢንተርኔት መኖር የተሳሳተ መረጃን በማሰራጨት ረገድ ሚና ተጫውቷል” ሲሉ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጉባኤው መክፈቻ ላይ የእገዳውን አስፈላጊነት ተከላክለዋል ሲል አሶስዬትድ ፕረስ ሪፖርቱን ደምድሟል።

XS
SM
MD
LG