በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያን የሰላም ጥረቶች እንደምታግዝ አንተኒ ብሊንከን ገለጹ


ዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

ዩናይትድ ስቴትስ፣ በኢትዮጵያ በውይይት ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን እንደምታግዝ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት፣ የደርግ/ኢሕዴሪ መንግሥት ወድቆ ኢሕአዴግ ሥልጣኑን የተቆጣጠረበት የግንቦት 20ን በዓል አስመልክቶ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት የመልካም ምኞት መግለጫ ነው፡፡

“ብሔራዊ ቀናችሁን በምታከብሩበት ዕለት፣ በዩናይትድ ስቴትስ ስም ለኢትዮጵያ ያለንን መልካም ምኞት ላቀርብ እወዳለሁ፤” ብለዋል ብሊንከን፡፡

ወቅቱ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 120ኛ ዓመት የሚከበርበትም እንደኾነ በመግለጫቸው ያወሱት ብሊንከን፣ በኢትዮጵያውያንና በአሜሪካውያን መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከርና ትስስሩን ማጥበቅ እንደሚያሻ አመልክተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ እገዛ ታደርግባቸዋለች ካሏቸው ጉዳዮች ውስጥ፥ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ደኅንነትን ማረጋገጥ፣ ጤናንና የአየር ንብረት ለውጥን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ችግሮችን በትብብር መፍታት የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

“የገጠሟችሁን ፈተናዎች ተቋቁማችሁ፣ ብሩህ ተስፋ ለመፈንጠቅ በያዛችሁትም ጥረት የአሜሪካ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ይቆማል፤” ያሉት የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ብሊንከን፣ “ይህን አጋጣሚም ምክንያት በማድረግ የአክብሮት መልካም ምኞቴ አደርሳለሁ!” ሲሉ፣ የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ቋጭተዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ የግንቦት 20ን በዓል በማስመልከት ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ፣ “ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. የትግራይ ሕዝብ ተጭኖበት የነበረውን ጭቆናና አፈና በማስወገድ በፍትሕ እና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዐዲስ ሕዝባዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ያካሔደው የትጥቅ ትግል በድል የተጠናቀቀበት ነው፤” ብሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG