በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

 
ለሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎች ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው ተለቀቁ

ለሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎች ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው ተለቀቁ


ለሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ እና የዋናውና የሕዝብ ግንኙት ኮሚቴውም አባል ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ዛሬ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው መለቀቃውን ተናግረዋል፡፡

(ይህ ገፅ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ኮምፕዩተርዎ ከአንድ በላይ ድምፅ ማጫወቻ አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ፅሁፍ ሥር ካሉት ማጫወቻዎች አንደኛውን ብቻ አስቀርተው ሌሎቹን ያቁሟቸው፡፡)

ኡስታዝ አቡበከርና ኡስታዝ አህመዲን ዛሬ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል አካባቢ ዘነበ ወርቅ እየተባለ በሚጠራው ሠፈር በመኪና እየተጓዙ ሣሉ ተይዘው ለአራት ሰዓታት ያህል እሥር ቤት ውስጥ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በጉዞ ላይ ሣሉ በአንዲት የግል ሠሌዳ ባላት ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ የሲቪል ልብስ የለበሱ ሰዎች አስቁመዋቸው ወደራሣቸው መኪና ካስገቧቸው በኋላ ወደአዲሱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕንፃ እንደወሰዷቸው ገልፀዋል፡፡

እዚያ እንደደረሱም በተናጠል ሁለት ሰዓት ለሚሆን ጊዜ በሁለት ባዶ ክፍሎች ውስጥ ካስቀመጧቸው በኋላ እንደዚያው በተናጠል ወደቢሮ እየጠሩ “እኛ የመጣነው ካንተ ጋር ልንወያይ አይደለም፤ ማስጠንቀቀያ ልንሰጥህ ነው፤ እየሆነ ባለው ሂደት ውስጥ ሁለን ነገር የምታደርገው አንተ ነህ፤ የምታደርገውን ነገር ሁሉ እናውቃለን፤ ከተቃዋሚዎች ጋርም ግንኙነት እንዳለህ እናውቃለን፤ ሁሉም መረጃ አለን፤ የምታደርጉትን፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የምትቀሰቅሱትን፤ ዓላማችሁ ዕምነት አይደለም፤ ፖለቲካ ነው” እንዳሏቸው አመልክተዋል፡፡

ሊሰሟቸውም ፍቃደኛ አለመሆናቸውንና የሚሰጧቸውም “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” መሆኑን፤ “ከእናንተ ጋር ፍርድ ቤት በመመላለስ የምናጠፋው ጊዜ የለም፤ የራሣችንን እርምጃ እንወስዳለን” ያሏቸው መሆኑን ሁለቱም በየራሣቸው ተናግረዋል፡፡

በኋላም ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ ቀደም ሲል በእሥረኛ ደንብ መሠረት የወሰዱባቸውን የግል ንብረቶቻቸውን መልሰውላቸው እንደለቀቋቸው አመልክተዋል፡፡

ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ሰዎቹ ካሣይዋቸው ማመናጨቅ፣ የኃይል ቃላትና ማስጠንቀቂያዎች ሌላ የደረሰባቸው የአካል ጥቃት አለመኖሩን ኡስታዝ አቡበከርና ኡስታዝ አህመዲን አመልክተዋል፡፡

ስለሁኔታው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትና ተፈጠረ የተባለውንም አጋጣሚ ለማረጋገጥ ብዙ ሙከራዎችን አድርጌአለሁ፡፡ ወደአዲስ አበባ ፖሊስና ተያዝን ወዳሉበት ኮልፌ ክፍለከተማ ፖሊስ ደውዬ የመረጃ ክፍል ባልደረቦችን አነጋግሬአለሁ፡፡ ስለሚባለው ሁኔታ ለጊዜው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልፀውልኛል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስን ሕዝብ ግንኙነት ለማግኘትም ጠይቄ ሕንፃው አዲስ ስለሆነ እና ቢሯቸው ውስጥም ስልክ ገና ስላልገባ ላገኛቸው እንደማልችል ተነግሮኛል፡፡

ወደአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በስልክ ቁጥር 011-1-568311 በተደጋጋሚና ለረዥም ጊዜ ደውዬ የሚያነሱት ሰው የውጭ ድምፅ አይሰማቸውም ይመስለኛል አዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መሆኑን ብቻ እየነገሩኝ ተዘግቷል፡፡

ወደፌደራል ፖሊስም የመረጃ አገልግሎትና የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ደውያለሁ፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ሁሉ ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ተነግሮኛል፡፡

ወደኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ወደ ኮሚሽነሩ ቢሮና ወደ ኢንፎርሜሽንና ኮምዩኒኬሽንስ ዳይሬክቶሬት ደውዬ ኃላፊዎች ሁሉ ስብሰባ ላይ መሆናቸውና ከሰኞ በፊት ላገኛቸው እንደማልችል፤ ላነጋግረው ወይም ዝርዝር ማብራሪያ ሊሰጠኝ የሚችልም ሰው እንደሌለ ተነግሮኛል፡፡

ጥረታችን ይቀጥላል፡፡ ማንኛውንም መረጃ ከየትኛውም ክፍል ባገኘን ጊዜ ይዘን እንመለሣለን፡፡

ዝርዝሩን የያዘውን ከሁለቱም ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

(ገፁ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ከማጫወቻዎቹ አንደኛውን ብቻ አስቀርተው ሌሎቹን ያቁሟቸውየሚጫወተውን እንደገና ያስጀምሩት፡፡ )


XS
SM
MD
LG