በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በየመን ባሕር ዳርቻ በተከሰተ የጀልባ አደጋ 20 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ሞቱ


ፍልሰተኞችን ይዞ ይጓዝ የነበረ ጀልባ በየመን ባሕር ዳርቻ ተገልብጦ 20 ኢትዮጵያውን ሕይወታቸውን እንዳጡ የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) አስታውቋል።

በአካባቢው የነበረው አደገኛ ነፋስ ባለፈው ቅዳሜ ለተከሰተው የጀልባ አደጋ ምክንያት እንደሆነ የገለጸው ድርጅቱ፣ ከጅቡቲ የተነሳ ሳይኾን አይቀርም በተባለው ጀልባ ላይ 35 ኢትዮጵያውያን ተሳፍረው እንደነበርና 15 የሚኾኑትና ሁለት የመናውያን የጀልባው ባለቤቶች ከአደጋው መትረፋቸውን አስታውቋል።

“አደጋው ፍልሰተኞች ደኅንነትና የተሻለ ሕይወት ፍለጋ አደገኛ ጉዞ በሚያደርጉበት ወቅት የሚያጋጥማቸውን አሳዛኝ ሁኔታ የሚያሳይ ነው” ሲሉ በየመን የአይ ኦ ኤም ተልዕኮ ኃላፊ አብዱሳቶር ኢሶየቭ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መደበኛ ላልሆነ ስደት ለሚዳርጉት መንስዔዎች መፍትሔ እንዲሻ እና ፍልሰተኞች ክብርና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ኃላፊው ጠይቀዋል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 2024 ብቻ 60 ሺሕ የሚኾኑ ፍልሰተኞች የመን መድረሳቸውን አይ ኦ ኤም አስታውቋል።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 2014 ወዲህ በምሥራቅ አፍሪቃ በኩል ባለው የፍልሰተኞች መንገድ 3ሺሕ 435 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG