በኒውዮርክ የሚገኘው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን CPJ የ2003 ዓ.ም. የአለም የመገናኛ ብዙሃን ሽልማትን ለአንድ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ሰጥቷል።
CPJ እንዳስታወቀው፤ የአውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ ከኢትዮጵያ ናዲራ ኢሳየቫ ከራሻ፣ ላውሬኖ ማርኩየዝ ከቪኔዙዌላ እና ሞሃመድ ዳቫሪ ከኢራን በጋዜጠኝነት ስራ ላበረከቱት አስተዋጾ ይህንን ታላቅ ሽልማት ሰጥቷቸዋል።
ሂውማን ራይትስ ወች የ2003 የሰብአዊ መብት ጠባቂ ሽልማትን ለቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ ዋና ጸሀፊ ዮሴፍ ሙሉጌታ የአመታዊው የአሊሰን ደ-ፎርዥ የሰብአዊ መብት ጠባቂ ሽልማት ተቀባይ መሆኑን አስታውቋል።
የሰብ አዊ መብት ይዞታን ተከታትሎ መመዝገብና መመርመር አስቸጋሪ በሆነባት ኢትዮጵያ ለሰራው ስራ የ36 አመቱን የመብት ተሟጋች መሸለሙን የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኬኒት ሮት ተናግረዋል። “በዚህ ሰው ታታሪነትና ጀግንነት ሁላችንም እንኮራለን” ብለዋል።
ለዚህ አመታዊ ክብር የበቁት ሌሎች የመብት ተሟጋቾች ከግብጽ ሆሳም ባጋት፣ ከራሻ አሌና ሚላሻና፣ ከካሜሩን ስቲቭ ነማንዴ፣ ከኢራን ሱዛን ታህማሴቢ እና ከቻይና ሉ ዥያቦ ናቸው።
ዮሴፍ ሙሉጌታ ከቪኦኤ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታን መዘገባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መሂዱን ተናግሮ፤ በቅርቡ በጸደቀው የሲቪል ማህብራት አዋጅ ሳቢያ ኢሰመጉ ገቢው በመዳከሙ ተንቀሳቅሶ የመስራት አቅሙ ተገድቧል ብሏል።
በመላው አገሪቱ የነበሩትን 13 ቢሮዎች ወደ 3 ዝቅ ለማድረግም ተገዷል።