የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ቅዳሜ ታኅሣስ 12 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የሀገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ምንጮች አስታውቀዋል።
ፕሬዝደንቱ በዋነኛነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ በመኾን፣ በሀገራቸው መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የታደሰውንና አዲስ አበባ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመንግሥት ወይም ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት መርቀው እንደሚከፍቱም ጠቅሰዋል።
የፈረንሳዩ መሪ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያካሂዱም እነዚሁ ምንጮች አመልክተዋል።
ምንጮቹ እንደጠቀሱት፣ ሁለቱ መሪዎች በቅድሚያ የሚወያዩት፣ በዚኽ ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል በቱርክ በተፈረመው የአንካራ ስምምነት ላይ ነው።
ፕሬዝደንት ማክሮን ስምምነቱን እንደሚቀበሉት በመግለጽ፣ ድጋፋቸውን እንደሚያሳዩም ዲፕሎማሲያዊ ምንጮቹ ጠቁመዋል።
ፕሬዝደንቱ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም በተመለከተ እንደሚነጋገሩና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚታዩ ግጭቶች አንጻርም ተመሳሳይ የሰላም መፍትሔዎችን እንደሚያበረታቱ ምንጮቹ አስረድተዋል።
ፈረንሳይ ቅዳሜ እንደሚመረቅ ለሚጠበቀው የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳት የ25 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጓን የፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ምንጮች ተናግረዋል።
ቤተ መንግሥቱ የቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ የብር ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ በ1948 ዓ.ም. የተገነባ ነው።
መድረክ / ፎረም