በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ ለመኸር ወቅት ከታረሰው መሬት አብዛኛው በዘር እንዳልተሸፈነ ተመድ አስታወቀ


በኢትዮጵያ ለመኸር ወቅት ከታረሰው መሬት አብዛኛው በዘር እንዳልተሸፈነ ተመድ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:02 0:00

በኢትዮጵያ ለመኸር ወቅት ከታረሰው መሬት አብዛኛው በዘር እንዳልተሸፈነ ተመድ አስታወቀ

በኢትዮጵያ የመኸር ወቅት አምራች በኾኑ አካባቢዎች፣ በዘንድሮው ወርኀ ክረምት፣ ማሳዎች ታርሰው ለዝሪት ዝግጁ ቢኾኑም፣ አብዛኞቹ በዘር እንዳልተሸፈኑ፣ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA) ሪፖርት አስታወቀ፡፡

ቢሮው፣ ትላንት ባወጣው ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ የወርኀ ክረምት የመኸር ወቅት አብቃይ የኾኑ አካባቢዎች፣ ማሳቸውን አርሰው እና አለስልሰው ቢያዘጋጁም፣ በዘር የተሸፈነ መሬታቸው አነስተኛ እንደኾነ አስታወቀ።

በአገሪቱ የመኸር ወቅት አምራች አካባቢዎች፣ መታረስ ካለበት መሬት፣ እስከ አሁን 80 በመቶው ታርሶ ለዝሪት ቢዘጋጅም፣ በዘር የተሸፈነው መሬት አነስተኛ እንደኾነ፣ ኦቻ፣ የግብርና ክላስተርን መረጃ ዋቢ በማድረግ ገልጿል፡፡

በዘር በተሸፈነው መሬት መጠን፣ በክልሎች መካከል ልዩነት እንዳለ የጠቆመው ኦቻ፣ ለአብነትም በዐማራ ክልል 50 በመቶ፣ በኦሮሚያ ክልል 80 በመቶ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 48 በመቶ፣ በደቡብ ክልል 50 በመቶ እና በትግራይ ክልል ደግሞ 30 በመቶው፣ የታረሰ መሬት እንደተዘራበት አመልክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚኾነው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የምግብ ድጋፍ እንደሚሻ የገለጸው ኦቻ፣ ቀጣዩ የምርት ኹኔታ በርዳታ ጠባቂው ሕዝብ ቁጥር ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ጠቁሟል፡፡

የዘር ወቅት እያለፈ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ሰፊ የእርሻ መሬት ላለመሸፈኑ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ የኾኑ ልዩ ልዩ ምክንያቶች፣ በኦቻ ሪፖርት ውስጥ ተዘርዝረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡- በኦሮሚያ እና በዐማራ አንዳንድ አካባቢዎች የተስፋፋው የጸጥታ ችግር እና የግብአት አቅርቦቶች መቀነስ፣ እንዲሁም እንደ ደቡብ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ፣ የጎርፍ መከሠት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ከመኸር ወቅት የግብርና ሥራ ጋራ በተያያዘ፣ በርካታ ችግሮች ካሉባቸው ክልሎች አንዱ የኾነው የትግራይ ክልል የግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የሰብል ልማት ዲሬክተር አቶ ሰሎሞን ገብረ ሥላሴ በሰጡን አስተያየት፣ ከአፈር ማዳበሪያ ግብአት መሟላት አንጻር፣ በተለይ ከዘር በፊት የሚያስፈልገው የማዳበሪያ ዐይነት ከተጠየቀው በእጅጉ ያነሰ መቅረቡን ገልፀዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ፣ ከግብርና ሚኒስቴር ሓላፊዎች አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ኾኖም፣ በቅርቡ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሡ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከፍተኛ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ክረምት ከታረሰው የመሬት መጠን፣ በሁለት ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጥ ማለትም 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬት፣ ዘንድሮ እንደሚታረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አመልክተዋል፡፡

በመላ አገሪቱ የሚታየው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ያጋጠመው፣ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት፣ ለዓለም አቀፍ ግብይት ክፍያ የሚፈጸምበት የኤልሲ ሒደት በጊዜ ባለመጠናቀቁ እንደኾነ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ግን፣ ግዢው ተፈጽሞ ማዳበሪያ እንዲገባ በመደረግ ላይ ነው፤ ብለዋል፡፡ ይኹንና፣ ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋራ በተያያዘ፣ መዘግየት መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልሸሸጉም፡፡

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ፣ በየቀኑ በአማካይ እስከ 20ሺሕ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ፣ ከጅቡቲ ወደብ ተነሥቶ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመሠራጨት ላይ እንደኾነ፣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ትላንት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ አርሶ አደሮች፣ ማዳበሪያ የሚጠቀሙበት የዘር ወቅት እያለፈባቸው እንደኾነ ገልጸው፣ ያለማዳበሪያ ዘር ለመዝራት እንደተገደዱ ቅሬታቸውን በማሰማት ላይ እንደኾኑ ይታወቃል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች፣ አርሶ አደሮች ሰልፍ ማድረጋቸውና በዚኽም ከጸጥታ ኃይሎች ጋራ መጋጨታቸው አይዘነጋም፡፡

/የዘገባውን ሙሉ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG