በኢትዮጵያ እና በኬንያ ደንበር ላይ በሚገኙ ዓሣ አሥጋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት፣ ከኢትዮጵያ በኩል ዐሥራ ሶስት፣ ከኬንያ በኩል ደግሞ ከሃያ በላይ ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁ ተገልጿል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ አስተዳዳር፣ በግጭቱ 13 ኢትዮጵያውያን መገደላቸውንና ከቤተሰብ አባላት ማረጋገጡንና እስከ አኹን የአንድ ሰው አስከሬን ብቻ መገኘቱን ሲያስታውቅ፣ ከኬንያ በኩል 22 የሚደርሱ ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን፣ የኬንያ ፖሊስ እና የመንግሥት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ካለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በዓሣ ማሥገሪያ መረብ ዝርፊያ የተነሣ፣ በዳሰነች እና በቱርካና አርብቶ አደሮች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ተካርሮ፣ ትላንት እሑድ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሰዎች መገደላቸውን፣ በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሀቴ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ ተናግረዋል።
በግጭቱ 22 የሚደርሱ ኬንያውያን አርብቶ ዐደሮች መጥፋታቸውን፣ የኬንያ ፖሊስ እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ማስታወቃቸውን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
ግጭቱ የተቀሰቀሰው፣ በኬንያ እና በኢትዮጵያ ደንበር አቅራቢያ በሚገኘው የኦሞ ወንዝ አካባቢ በሚገኙት ሎፐሙካት እና ናቲራ በተባሉ ስፍራዎች እንደኾነ፣ የኬንያ ቱርካና አውራጃ አስተዳዳሪ ጀረማያ ሎሞሩካይ፣ ትላንት እሑድ በሰጡት መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል።
በዚኹ ግጭት፣ 15 ጀልባዎች መሰረቃቸውንና ከኢትዮጵያ ወገንም የዳሰነች ብሔረሰብ ተወላጅ የኾኑ ስድስት ዓሣ አጥማጆችን ታድገው ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን፣ የቱርካና አውራጃ ፖሊስ አብራርቷል።
የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮሜን፣ በኤክስ የትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት፣ መንግሥት ትላንት እሑድ ተጨማሪ ኀይል ወደ ደንበር እንዲሰማራ ማድረጉን ጠቅሰዋል፤ በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል ሰላምን ለማስፈን፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ እንደሚነጋገርም ጠቁመዋል።
መድረክ / ፎረም