በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ሳንሱር በአፍሪቃ መሪ አገር ሆና ቆይታለች ሲል ሲፒጄ አስታወቀ


ቴክኖሎጂ ሳንሱር በምሥራቅ አፍሪቃ እያደገ ነው በማለት የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋቹ ድርጅት - ሲፒጄ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል።

በዚህ የነፃ መረጃዎች ሳንሱር ቴክኖሎጂ ቅድምያ የያዘችው ኢትዮጵያ መሆኗን በመጥቀስ ሌሎች ድርጅቱ አምባገነን ሲል የገለፃቸው የአካባቢው መንግሥታት ይህን አሉታዊ ፈለግ እንዳይከተሉ ሥጋቱን ገልጿል።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2005 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ሌሎች አገሮች ዘገባዎች እንዳይታፈኑ የኢንተርኔት አገልግሎት ትልቅ አስተዋጽዖ ሊያደርግ እንደሚችል ገና በግንዛቤ ደረጃ ላይ እንዳሉ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መንግሥት ዋና ዋና የኢንተርኔት ዘገባዎችና የ “ዶት ኮም” ገፆች እንዳይነበቡ ሲጋርድ ነበር።

የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋቹ ድርጅት የኢንተርኔት አድቮኬሲ አስተባባሪ ዳኒ ኦብራያን ዛሬ ለቪኦኤ በሰጠው መግለጫ የመንግሥቱ ሳንሱር ሊያተኩርባቸው የሚችል የኢንተርኔት አድራሻዎችን ጠቁሟል፡፡

“ለእኛ አሣሣቢ የሆኑት ዌብ ሣይቶች በስደት ውጭ ያሉ ጋዜጠኞች የሚዘግቡባቸው ለምሣሌ እንደ አዲስ ነገር፣ የአውራምባ ታይምስና ኢትዮጵያን ሪቪው ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ስለኢትዮጵያ ነፃ መረጃዎችን የሚያቀርቡ ቢሆንም አገር ውስጥ እንዳይነበቡ የተጋረዱ ናቸው፡፡ ይህ ለረዥም ጊዜ የተካሄደ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን እየወሰደ ያለው አዲስ እርምጃ የግለሰቦችን የፌስቡክ ገፅ ማገድ ነው፡፡ እንዳልኩት ብዙ ኢትዮጵያዊያን የሚጠቀሙባቸው ቶርን የመሣሰሉ ሶፍትዌሮችና የኢንተርኔት መገናኛ ዘዴዎች ሳንሱር እየተደረጉ ነው” ብሏል ኦብራያን፡፡

በአሁኑ ዓመት የኢትዮጵያ መንግሥት ከቀድሞው በተሻለ የረቀቀ ቴክኖሎጂ የኢንተርኔት ዌብ ሣይቶችን መሸፈንና ማገድ እንደጀመረ ታዛቢዎች እንደሚናገሩ ሲፒጄ አመልክቷል።

ካለፈው ሚያዚያ ጀምሮ “ደ ብርሃን” የተባለውን የዜናና የትንታኔ ዌብ ሣይት ጨምሮ ፅሁፎችን በኢንተርኔት የሚያወጡ በርካታ ዘጋቢዎች ፅሁፎቻቸው እንዳይታዩ በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚጋረዱ ተናግረዋል።

አንዳንድ ከአገር ውጪ የሚኖሩ ጋዜጠኞች እንደጠቆሙት በኢትዮጵያ መንግሥት አልፎ አልፎ የሚጋረዱ ዌብ ሣይቶች ቁጥር እየጨመረ ነው። ለምሳሌ “We All Are Eskinder Nega” [“ሁላችንም እስክንድር ነጋ ነን”] ከሚለው የግል የfacebook ገፅ ጋር አብረው ብዙ ገፆች ተጋርደዋል።

ኢትዮጵያ የኢንተርኔት ፅሁፍ ሳንሱር እንዳይደረግ የሚከላከሉና የኢንተርኔት ፀሐፊዎችን ማንነትና አድራሻ የሚያጠፉ ወይም የሚደብቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የያዙ አገልግሎቶችን ሁሉ እያገደች መሆኗን “ዘ ኦንየን ራውተር ፕሮጀክት” ወይም በምኅፃር “ቶር ፕሮጀክት” የሚባለው የኢንርኔት የግል መረጃ ደባቂ አገልግሎት ገልጿል፡፡

ቶር የኢንተርኔት ምልልሱን ገፅታ መለወጥና መተርጎም፣ አንዳንድ ጊዜም ደሕንነቱ እንደተጠበቀ የኢንተርኔት አውታር እንቅስቃሴ ሆኖ ይሠራል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የተለዩ የኢንተርኔት አሠራሮችን እያወጣች ሳንሱር እንደምታደርግና እንደምታግዳቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቶር የኢንተርኔት አውታር እንቅስቃሴ አሁን ካለፈው ግንቦት ከነበረበት ስፋት በእጅጉ የቀነሰ ሲሆን ተመልሶ የማንሠራራት አዝማሚያም አይታይበትም፡፡

ሲፒጄ በመግለጫው ላይ “ይህ ሁሉ ታዲያ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አገዛዝ ለምሣሌ ፌስቡክን የመሳሰሉ አገልግሎቶችን እንዳሉ ከማገድ ይልቅ የተወሰኑ የፌስቡክ ቡድኖችን ወይም የኢንተርኔት አገልግሎቶች ዓይነቶችን ለይቶ ለማፈን እንደሚችል መተማመን አሳድሮበታል” ብሏል፡፡

በድምፅ የተደገፉና (በምኅፃር “ቪኦአይፒ” ይባላሉ) ስካይፕን የመሣሰሉ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ሕገወጥ ያደርጋል የተባለው ሕግ የኢትዮጵያ መንግሥት አዳዲሶቹን አቅሞቹን ተግባራዊ ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑን ያሣያል ሲል ሲፒጄ አመልክቷል፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚያን በድምፅ የተደገፉ መልዕክቶችን መለዋወጫ አገልግሎቶችን ወይም ቪኦአይፒዎችን በተናጠል ያግድ ወይም ይዘጋ እንደነበር የቢቢሲዋ የቀድሞ የኢትዮጵያ ዘጋቢ ኤሊዛቤጥ ብላንት አመልክታ አዲሱ ቴክኖሎጂና አዲሱ ሕግ ተቀናጅተው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለውን የቴሌፎን አገልግሎት ሊሻሙ በሚችሉ የኢንተርኔት አሠራሮች ላይ መንግሥቱ ጥቅል እቀባ ለመጣል እንደሚያስችለው ገልፃለች፡፡

“እኔ እንደማምነው ኢትዮጵያዊያን ከሚዘወተረው ሞባይል ወይም ከቤት ቴሌፎን ውጭ ምንም እንዳይጠቀሙ ነው፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች መንግሥት እራሱ ወይም ቴሌኮም የተባለው ተቋሙ እንደሚቆጣጠረው ይታወቃ” ብሏል የሲፒጄው ኦብራያን ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገር፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ እነዚያን በድምፅ የሚደገፉ ስካይፕና የመሣሰሉትን ከኢንተርኔት የሚገኙ አገልግሎቶችን ልትዘጋ ነው መባሉን የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሺመልስ ከማል “ሃሰት ነው” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ “እንዲህ ዓይነቱ ሃሣብ - አሉ አቶ ሺመልስ በቀድሞም በአሁኑ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ የሉም፡፡”

አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚዘጋቸው ያልገለፃቸው ወይም ሊዘጋቸው አቅሙ የሌለው የኢንተርኔት አገልግሎቶች እንዳሉ የሚናገረው የሲፒጄ መግለጫ ግን ምንም እንኳ የተናጠል የፌስቡክ ገፆችን ሳንሱር ማድረግ ቢችልም ተጠቃሚዎች የፌስቡክን የሳንሱር ማስወገጃ ዘዴ ከራሱ ከፌስቡክ ከተጠቀሙ ሊታገዱ ወይም ሊታዩም እንደማይችሉ ይመክራል፡፡

ምንም እንኳ አንዳንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊዘጋቸው ወይም ሊያግዳቸው እየቻለ ያልዘጋቸው አገልግሎቶችን የተዋቸው አንድም የኢኮኖሚ ወይም የፖለቲካ ወይም ሌላ መዘዝ ያላቸው ናቸው ብሎ ስለሚያምን መሆን እንዳለበት ሲፒጄ አመልክቷል፡፡

ሲፒጄ መግለጫ ያወጣበት ይህ በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ እገዳና ሣንሱር የሚያሣድር አሠራር ቀዳሚው ዓላማ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ መሆኑን የሲፒጄው የአድቮኬሲ አስተባባሪ ዳኒ ኦብራያን አመልክቷል፡፡

“በድምፅ አገልግሎት ረገድ ቀዳሚው ዓላማቸው የኢኮኖሚ ጥቅም እንደሆነ አምናለሁ። ዋናው ዓላማ የመንግሥት ከሆነው የቴሎኮም አገልግሎት ጋር ምንም የንግድ ውድድር እንዳይኖር ነው። ሆኖም ግን ተጠቃሚው ሁሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለው ቴሊኮምን እንዲጠቀም ማስገደድ፣ መንግሥት ግንኙነቶችን ሁሉ እንዲከታተልና እንዲቆጣጠር ያደርጋል። በዚያውም ተጠቃሚዎች እንዳይገናኙ ለማድረግም ያስችለዋል ማለት ነው” ብሏል ኦብራያን፡፡

“ዘ ኦንየን ራውተር” ወይም በምኅፃር “ቶር ፕሮጀክት” ኢንተርኔትን ሣንሱር ማድረግን አዳጋች የሚያደርጉ ሌሎች አሠራሮችን ለመፍጠር በርትቶ እየሠራ እንደሆነ ይኸው የሲፒጄ መግለጫ አመልክቶ ከኢትዮጵያ የሚወጡ ሳንሱር ያልነካቸው ዜናዎች የሚገኙበት ቀዳዳ ግን አሁንም ጠባብ እንደሆነ አክሎ ገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እጅግ ኋላ ቀር በሆነ የሳንሱር አሠራር፣ የገዛ ዜጎቿን ያለአባብ በማሠርና በግድ እንዲሰደዱ በማድረግ የምታተወቀው የኢትዮጵያዋ ጎረቤት ሱዳን ውስብስብ የሆነውን የቁጥጥር አሠራር ከጎረቤትዋ ልትቀዳ እንደምትችል ሥጋት ማሣደሩን ሲፒጄ አክሎ አመልክቷል፡፡

“ኢትዮጵያ የምታስገባቸውና ሥራ ላይ የምታውላቸውን ማንኛቸውንም ዓይነት የኢንተርኔት አፈና አሠራሮችን ሌሎች የአፍሪካ አምባገነን አገዛዞች እንደሚወርሷቸው ጥርጥር የለም” ብሏል ሲፒጄ፡፡

ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ፡፡

(ገፁ ሲከፈት የተደራረቡ ወይም የተረበሹ ድምፆችን የሚሰሙ ከሆነ ከማጫወቻዎቹ አንደኛውን ብቻ አስቀርተው የቀሩትን ያቁሟቸው፡፡)


XS
SM
MD
LG