ዋና ፅ/ቤቱ ለንደን የሚገኘው ሂዩማን ራይትስ ዋች የሚባለው ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ጥቅምት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከውጭ ለጋሾች የሚያገኙትን እርዳታ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለማይስማሙት በመንፈግ በመደበኛነት እንደመሣሪያ ይጠቀምበታል ብሏል፡፡
የድርጅቱ መርማሪና ጉዳይ አጥኚ ቤን ሮውለንስ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት መግለጫ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ለእነዚህ ገበሬዎችና የቀበሌ ነዋሪዎች "እርዳታ ለምን የራሣችሁ ፓርቲ ዘንድ ሄዳችሁ አትጠይቁም? ይህ ገዥው ፓርቲ ከዓለም ታግሎ ያመጣው ነው፤ የሚያውለውም ለራሱ ነው" እንደሚሏቸው አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም የልማት ልገሣ ዋነኛ ከሚባሉት ተጠቃሚዎች መካከል እንደምትገኝ የጠቀሰው ዘገባ በመሪነት ዩናይትድ ስቴትስ፣ እንግሊዝና ጀርመን ካሉበት የለጋሾች ቡድን በ2008 ዓ.ም. (እ.አ.አ) የሦስት ቢልየን ዶላር እርዳታ ማግኘቷንም አመልክቷል፡፡
የአሁኑን መንግሥት የመሠረተው ፓርቲ ባለፈው ግንቦት በተካሄደው ምርጫ እጅግ የገነነ ድል መቀዳጀቱን ሪፖርቱ አስታውሶ የምርጫው ውጤት "በሃገሪቱ ያለው የከበደ የፖለቲካ አፈና መገለጫ ትኩሣትና ቁርጠት የሚስተዋሉበት ነው" ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዉ መንግሥትን ተቃውሞ መናገር እንደሚፈራ የሚጠቁሙት ሮውለንስ "አገዛዙ አፈና እጅግ የበዛበት፣ እያንዳንዱ አምስት አባወራ ለቀበሌው የፓርቲ ሊቀመንበር የሚጠራበት፣ የቀበሌውም ለበላዩ፣ እንዲህ እያለም እስከላይ የሚዘልቅበት በተጠናከረ ሥርዓት የታጠረ የቻይናውን ማዖይስት ዓይነት ዘይቤ ያለው ነው" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን መንግሥት "የከበደ አፈና" በሚለው ክሱ የሚወቅሰው ሂዩማን ራይትስ ዋች ለጋሾች ለዚህ መንግሥት እርዳታ ሲሰጡ ተጠያቂነትና ግልፅነት እንዲኖረው፣ ገንዘባቸው ለአፈና ተግባር እንደማይውል ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው አሳስቧል፡፡
የሃገሪቱን ልማትና ዕድገት እንዲያፋጥን ከመንግሥታት የሚሰጠውን የአቅም ግንባታ ድጋፍም የኢትዮጵያ መንግሥት "የትምህርት ቤት ሕፃናትን በፓርቲው አስተሣሰብ ለማጥመቅ፣ መምህራንን ለማሸማቀቅ፣ በፃ የፖለቲካ አስተሣሰብ ያላቸውን ሲቪል ሠራተኞች ከሥራቸው ለማፈናቀልና ለማባረር ተግባር ያውለዋል" ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የልማት እርዳታ ኢትዮጵያ ውስጥ "ለገንቢና ለአዎንታዊ ሥራ እንደዋለ የሚገልፁት በኦስሎ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ፕሮፌሰሩ ክትጀል ትራቮል "ክሊኒኮችና ሆስፒታሎችን የመሣሰሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ መሠረታዊ ትምህርት ተስፋፍተዋል፤ ገንዘቡ ለመንገድና ሌሎችም የመሠረተ-ልማት አውታሮች ግንባታ ውሏል፤ ጠቃሚ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡" ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታው ገንዘብ በልማት መርኃግብሮቹ እንዲደርስ ስለማይፈቅድ ለጋሾች አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገኙ የኦስሎ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ተናግረው ድምፃቸውን ግን ከፍ አድርገው መጮኽ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዋች ይህንን ሪፖርት ሲያጠናቅር በሃምሣ ሦስት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ከሁለት መቶ በላይ ሰዎችን ለናሙና ወስዶ ቃለ መጠይቅ ያደረገ ሲሆን ለምርመራውና ሙሉውን ሪፖርት ለማዘጋጀት ባለፈው የአውሮፓዊያን ዓመት ስድስት ወራት እንደወሰዱበት ታውቋል፡፡ ለተጨማሪ ዝርዝር ዘገባውን ያድምጡ፡፡