በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የመንግሥት የወጪ ቅነሳ ፖሊሲ ማኅበራዊ ልማትን ሊጎዳ እንደሚችል ባለሞያዎች ጠቆሙ


 የመንግሥት የወጪ ቅነሳ ፖሊሲ ማኅበራዊ ልማትን ሊጎዳ እንደሚችል ባለሞያዎች ጠቆሙ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:35 0:00

የመንግሥት የወጪ ቅነሳ ፖሊሲ ማኅበራዊ ልማትን ሊጎዳ እንደሚችል ባለሞያዎች ጠቆሙ

ይህ ፖሊሲ፣ ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች በሚያደርጓቸው ግፊቶች መንግሥት ከተገበራቸው የፖሊሲ ለውጦች መካከል አንዱ እንደኾነ የሚናገሩት ባለሞያዎቹ፣ ጋናን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ቢተገበርም ውጤት ማምጣት ያልቻለ ነው፤ ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ምንም ዓይነት ሜጋ ፕሮጀክት እንዳልጀመረ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ ይህም በወጪ ቅነሳ እና የገንዘብ ፍሰቱን በማስተካከል የዋጋ ንረትን ለመገደብ ያለመ እንደኾነ አመልክቷል።

ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ለሚሰጧቸው ብድሮች ከሀገራት ጋራ በሚያደርጓቸው ድርድሮች ከሚያነሧቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎች መካከል አንዱ፣ የመንግሥት ወጪ ቅነሳን እንደሚመለከት የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ይናገራሉ። ይህም መንግሥት፣ በዓመቱ ከሚይዘው በጀት በተወሰኑት ዘርፎች ላይ ቅናሽ ማድረግ ወይም ፕሮጀክቶችን ማጠፍ እንደማለት ነው።

የኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ባለሞያው አቶ ያሬድ ኀይለ መስቀል፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ባላደጉ ሀገራት፣ ይህን ፖሊሲ መተግበር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፤ ይላሉ። ኾኖም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን የፖሊሲ አማራጭ መተግበር መጀመሩን ይናገራሉ። ነዳጅን ጨምሮ ድጎማ የተነሣባቸውን ዘርፎች በማሳያነትም ይጠቅሳሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱን ወቅታዊ ኹኔታ አስመልክቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጧቸው ማብራርያዎች፣ መንግሥት በወጪ ቅነሳ ላይ አተኩሮ እንደሚሠራና የተጀመሩትን ከማጠናቀቅ በቀር ዐዲስ ፕሮጀክቶችን እንደማይጀምር በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ ይህም የመንግሥትን ወጪ ቀንሶና የገንዘብ ፍሰቱን አስተካክሎ የዋጋ ንረትን ለመገደብ ያለመ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማኅበር ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ዶክተር አረጋ ሹመቴ፣ እንዲህ ዐይነት የፊሲካል ፖሊሲ ርምጃዎችን፣ መንግሥታት፣ ኢኮኖሚን ለማረጋጋት ወይም እንደ ማነቃቂያ እንደሚወስዷቸው ያስረዳሉ፡፡

ፖሊሲው፣ የዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች በሚያደርጓቸው ግፊቶች መንግሥት ከተገበራቸው የፖሊሲ ለውጦች መካከል አንዱ እንደኾነ የሚገልጹት አቶ ያሬድ ኀይለ ማርያም፣ ይኹንና ጋናን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በሥራ ላይ ውሎ ውጤት ማምጣት ያልቻለ ነው፤ ይላሉ፡፡

ይህ “ወገብህን አጥብቅ ወይም በዓቅምህ ኑር” የሚለው ፖሊሲ፣ በተለይም ለአገሪቱ እድገት ወሳኝ የኾኑ እንደ ትምህርት እና ጤና ያሉ ዘርፎችን እንደሚጎዳም ያመለክታሉ፡፡

የዘንድሮውን በጀት በተመለከተ በገንዘብ ሚኒስቴር በተዘጋጀው ሰነድ ላይ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ባጋጠመው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ የወጪ ፍላጎት በመፈጠሩ ይህን ለማስተካከል ከተደረገው ማሸጋሸግ በቀር፣ ለትምህርት እና ለጤና የተመደበው ገንዘብ በቂ እንደኾነ ያትታል፡፡ የካፒታል በጀት ግን እየቀነሰ መምጣቱን ሰነዱ ያስረዳል፡፡

መንግሥት ይህን የወጪ ቅነሳ ያደረገው፣ በአስገዳጅ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ነው፤ የሚሉት ዶክተር አረጋ ሹመቴ፣ አሁን ባለው አገራዊ ነባራዊ ኹኔታ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ያስገነዝባሉ፡፡

ከዚህ በፊት በሥራ ላይ የዋሉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በአገሪቱ ላይ የፈጠሩት ችግር መኖሩን ያወሱት ዶክተር አረጋ፣ አሁንም ይህ እንዳይከሠት መጠንቅቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሁሉም ወጪዎች በርግጥም ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ስለመዋላቸው ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደኾነም ይናገራሉ፡፡

ዐሥር ወራትን ባስቆጠረው የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከተመደበው 801 ቢሊዮን ብር መካከል፣ ለፌደራል መንግሥት መደበኛ ወጪ የተመደበው 370ነጥብ14 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

አብዛኛው ወጪም “ለዕዳ ክፍያ፣ የሀገር ደኅንነትን ለማስጠበቅ፣ በጦርነቱ እና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች የዕለት ርዳታ ለማቅረብ እና ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ድጎማ” እንደሚውልም ሰነዱ ያሳያል፡፡

ከአጠቃላይ በጀቱ ለካፒታል ወጪዎች የተመደበው በጀትም፣ ካለፈው ዓመት የ6ነጥብ7 በመቶ ቅናሽ እንዳለው፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የበጀት ሰነድ ላይ ተመላክቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG