አሜሪካ የውጪ ርዳታዋን ማቁረጧ በኢትዮጵያ በርካታ የልማት ሥራዎችን፣ በተለይም ደግሞ ከኤችአይቪ ጋራ የሚኖሩ ሰዎችን ለመርዳት የሚደረገውን ጥረት እንደሚጎዳ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤች አይ ቪ ኤድስ ፕሮግራም (ዩኤሴይድስ) አስታውቋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከኤችአይቪ ጋራ የሚኖሩ የ503 ሺሕ ሰዎች በ1ሺሕ 400 ጤና ጣቢያዎች በኩል አንቲሪትሮቫይራል የተሰኘው መድኃኒት እንደሚሰጣቸው የተመዱ የኤድስ ፕሮግራም አስታውቃል።
በክልሎች የሚገኙ የጤና ባለሥልጣናት በአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤሴይድ) እና በአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) የገንዘብ ድጋፍ የሚሠሩ የጤና ሠራተኞችን እንዲያሰናብቱ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መመሪያ እንደደረሳቸው ለቪኦኤ አስታውቀዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከቪኦኤ አስተያየት እንዲሰጥ ተጠይቆ መልስ አልሰጠም።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ለውጪ ሃገራት የሚሰጥ ርዳት እንዲቋረጥ ማዘዛቸውን ተከትሎ፣ የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤችአይቪን ጨምሮ ሌሎችም ሕይወት አድን ፕሮግራሞችን አሜሪካ መደገፍ እንደሚቀጥል አስታውቆ ነበር።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ርዳታ እንደሚቀጥል ቀደም ብለው አስታውቀው የነበረ ሲሆን፣ ቆየት ብለው ደግሞ ደግሞ ሕይወት አድን መድሃኒቶችና የሕክምና አገልግሎቶች እንዲሁም የምግብና የመጠለያ ርዳታዎች እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም