ዕድሜያቸው ያልደረሰን ልጆች አስገድዶ ውትድርና ውስጥ ማስገባት በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ በጥብቅ የተከለከለ መኾኑን ያስገነዘቡ አንድ የሕግ ባለሞያ፣ መንግሥት እንዲህ ዐይነት ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል እንደሚገባው አሳስበዋል። የሕግ ባለሞያው አቶ ቁምላቸው ዳኜ፣ ዕድሜያቸው ያልደረሱ አዳጊ ልጆችን በውትድርና ውስጥ ማሳተፍ በኢትዮጵያም ኾነ በዓለም አቀፍ ሕግ በወንጀል የሚያቀጣ ተግባር መኾኑን ተናግረዋል። “መንግሥት በእርሱ አደረጃጀ ብቻ ሳይኾን ከመንግሥት ጋራ የሚዋጉ ቡድኖችም እንዲህ ያለ ተግባር እንዳይፈጽሙ ለማድረግ ግዴታ ገብቷል” ብለዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም በአወጣው ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል ፣ ከ11 ዓመት እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አዳጊዎች፣ ከሕግ አግባብ ውጭ ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት እየተያዙ መኾናቸውን ማረጋገጡን አስታውቆ ነበር።
ኮሚሽኑ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአወጣው ተከታይ መግለጫ ደግሞ፣ በምርመራ ግኝቶቹ ላይ ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ እና ከውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እና አባላት ጋራ ውይይት ማድረጉን አስታውቋል።
መከላከያ ሚኒስቴር ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የምላሽ ደብዳቤ እንደጻፈለት የጠቆመው ኮሚሽኑ፣ በሁሉም ክልሎች የሚከናወኑ የሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሕግ በተቀመጡት መስፈርቶች መሠረት ብቻ የተከናወኑ ስለመኾናቸው በማረጋገጥ የሚረከብ መኾኑን እንደገለጸለት በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
መከላከያ መስፈርቱን ብቻ የሚያሟሉትን መርጦ ማስገባቱን፣ በሂደቱ ያጋጠመ ችግር ካለም የሚመለከተው መኾኑን ማስታወቁን ኮሚሽኙ ገልጿል። ክልሉ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ እና በቀጣይ ተመሳሳይ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለማድረግ የሚያስችሉ ርምጃዎችን እንዲወስድ ውትወታውን እንደሚቀጥልም አጽንኦት ሰጥቶበታል።
የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸውና በደኅንነት ስጋት ምክንያት ማንነታቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቄለም ወለጋ ጊዳም ወረዳ አርሶ አደር፣ ከፍቃዳቸው ውጭ ተይዘው የሚገኙ ሁለት ወንድሞች እንዳሏቸው ተናግረዋል። በተመሳሳይ የደኅንነት ስጋት ምክኒያት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አድን ግለሰብ በበኩሉ፣ ጓደኞቹ ሲያዙ ተመልክቶ እርሱ ማምለጡን ገልጿል።
የሕግ ባለሞያው አቶ ቁምላቸው ዳኜ፣ መንግሥት ዓለም አቀፉን የዘፈቀደ እስር መብት እና የሕጻናት መብት ረገጣ ስምምነቶችን በማክበር፣ በጉዳዩ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ኃላፊዎችና የክልል ሚሊሻዎችን በይፋ ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥትም ኾነ ከመከላከያ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ እስካኹን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም። የአሜሪካ ድምጽ በጉዳዩ ላይ ከተለያዩ የፌደራልና የክልል መንግሥት ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠናቀረውን ዘገባ ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም