በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያና ኤርትራ በወባ ላይ ስኬት ማስመዝገባቸውን ገለፁ


በኢትዮጵያ ወባን ለመከላከል የተያዘው ጥረት ፍሬ ማስገኘቱን፣ በኤርትራ ደግሞ ወባ ከእንግዲህ የሃገሪቱ ሥጋት አለመሆኑን ሃገሮቹ አስታውቀዋል፡፡

የወባ ቀን ዛሬ በመላው ዓለም ታስቦ የዋለ ሲሆን ዕለቱ በኢትዮጵያና በኤርትራ ውስጥም ታስቦ መዋሉን በኢትዮጵያ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩን አቶ አሕመድ ኢማኖ፣ በኤርትራ ደግሞ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የብሔራዊ የወባ መከላከያ ኃላፊ ዶ/ር ተወልደ ገብረመስቀል ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዛሬውን የዓለም የወባ ቀን አስባ የዋለችው “ያገኘናቸውን ውጤቶች ቀጣይነት እናረጋግጥ፣ በወባ ምክንያት የሚደርሰውን ሞት ለመከላከል እንረባረብ” በሚል መርኅ ነው፡፡

ሥነ-ሥርዓቱ የተከናወነው በቤንሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ርዕሰ ከተማ አሶሣ ሲሆን ዕለቱ ከአዲስ አበባ ውጭ ታስቦ ሲውል የአሁኑ ከካቻምናው የኦሮሚያና ከአምናው የትግራይ ቀጥሎ ሦስተኛው መሆኑ ነው፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ወባን በመከላከል የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ሦስት ሦስት ወረዳዎች ከየክልሉ የምሥክር ወረቀት ያገኙ ሲሆን በልማዱ መሠረት በመታሰቢያው ዕለት ዋዜማ ትናንት የተከናወኑ ተግባራትን ደካማና ጠንካራ ጎኖችን የገመገመ ስብሰባ እዚያው አሶሣ ውስጥ ተካሂዲል፡፡

ከ1997 ዓ.ም ወዲህ በተደረጉት ጥረቶችም በወባ ምክንያት ወደ ጤና ተቋማት የሚሄደውና የሚመላለሰው ሰው ቁጥር በ67 ከመቶ፤ የሞቱ መጠን ደግሞ በ54 ከመቶ መቀነሱን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በመከላከሉ ሥራ ውስጥ የሕብረተሰቡ ዕውቀትና ተሣትፎ መጨመሩን፣ አካባቢን በንፅህና የመያዝ ጥረት መጠናከሩን የጤና ልማት ሠራዊት የሚባሉ ሠራተኞች በየመንደሩ የሚሠጡት አገልግሎት መስፋቱን ገልፀው ቁጥፍ የሆነውን ሚና ተጫውቷል ባሉት የአጎበር ሥርጭት ከታቀደው ከዕጥፍ በላይ ጨምሮ 43 አጎበር መሠራጨቱንና ከአጠቃላዩ ሕዝብ 85 ከመቶ የሚሆነው ተጠቃሚ መሆኑን አቶ አሕመድ አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራ ውስጥም ወባን ለመከላከል በአውሮፓ የዘመን አቆጣጠር ከ2000 ዓ.ም ወዲህ እየተከናወነ ያለው ሥራ የተጠናከረ በመሆኑ የወረርሽኙ መጠን መቀነሱንና ወባ ከእንግዲህ ኤርትራ ውስጥ ሥጋት አለመሆኑን በኤርትራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የብሔራዊ የወባ መከላከል ኃላፊ ዶ/ር ተወልደ ገብረመስቀል ዛሬ ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡

ከ2000 ዓ.ም በፊት ከሁለት መቶ እና ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ሰው በወባ ይታመም እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ተወልደ አሁን በወባ የሚያዘው ሰው ግን ከሃምሣ ሺህ፤ የሚሞተውም በዓመት ከነበረው አምስት መቶ ወርዶ ከአሥር ሰው እንደማይበልጥ አመልክተዋል፡፡

የዝናብ ወቅት እየቀረበ በመሆኑም ከአንድ ሚሊየን በላይ አጎበር መሠራጨቱንና በቂ መድኃኒትም ያስፈልጋቸዋል ለሚባሉ አካባቢዎች መላካቸውን ዶ/ር ተወልደ አክለው ገልፀዋል፡፡

እአአ በ2010 ዓ.ም ከዓለም ሕዝብ ግማሽ የሚሆነው ወደ 3.3 ቢሊየን ሰው ለወባ የተጋለጠ እንደነበረ የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡ ይህ መስፋፋት ደግሞ 210 ሚሊየን ሰው የወባ ታማሚ እንዲሆንና 665 ሺህ በዚያው ዓመት ብቻ በወባ ምክንያት ለሞት መዳረጉን የድርጅቱ መግለጫ አመልክቷል፡፡

ለተጨማሪና ዝርዝር መረጃ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG