በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

«በአብዛኛው ታዛቢዎቻችን በሌሉበት ተካሄደ፤» ሲሉ፥ የገለፁት የግንቦት 15ቱ ምርጫ እንዲደገም ሁለት ዋነኛ ተቃዋሚ ቡድኖች አስታወቁ።


«የምርጫው ሂደትም ሆነ የድምፅ መስጫው ቀን፥ ነፃና ፍትሃዊ ባለመሆናቸው፤ ታዛቢዎቻችን ተደብድበው በመባረራቸው በብሄራዊው የምርጫ ቦርድ ይፋ የተደረገውን ውጤት አንቀበልም።» - መኢአድ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትና የኢትዮጵያ ፌድራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ዛሬ በተከታታይ በሰጧቸው መግለጫዎች በምርጫ ቦርድ ይፋ የተደረገውን ውጤት እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።

ምርጫ ቦርድ ውጤቱን ይፋ ካደረገና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም ድሉን ማክበር ከጀመረ በኋላ የመጀመሪያው በሆነው ይፋ የተቃዋሚዎች መግለጫ ሁለቱ ተቃዋሚ ቡድኖች ውጤቱን የማይቀበሉበትን ምክኒያትና አማራጭ ያሉትን በመግለጫቸው ዘርዝረዋል።

«የምርጫው ሂደትም ሆነ የድምፅ መስጫው ቀን፥ ነፃና ፍትሃዊ ባለመሆናቸው፤ በመላው አገሪቱ በሚገኙ አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎችም ታዛቢዎቻችን ተደብድበው በመባረራቸው በብሄራዊው የምርጫ ቦርድ ይፋ የተደረገውን ውጤት ላለመቀበል ወስነናል፤» ሲል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት በውጭ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ያቆብ ልኬ አማካኝነት አስታውቋል።

ይሄንን ውሳኔውን ትላንት ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ለምርጫ ቦርድ ማሳወቁን የገለፀው መኢአድ፥ የህዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫዎችም በተቻለ ፍጥነት በድጋሚ እንዲካሄዱ መጠየቁን አመልክቷል።

ኢህአዴግን አሸናፊ ያደረገውንና በቦርዱ ይፋ የሆነውን ውጤት እንደማይቀበል ከመኢአድ በተመሳሳይ ዛሬ ከቀትር በኋላ ያስታወቀው የስምንቱ ተቃዋሚ ቡድኖች ጥምረት መድረክ በበኩሉ፥ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ አገርና ታዛቢዎች፤ በተገኙበት ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ጠይቋል።

«ከኢህአዴግ ሌላ ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ የማይፈልግ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊኖር አይችልም፤» ብሎ እንደሚያምን መድረክ በሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አማካኝነት መድረክ ገልጧል።

XS
SM
MD
LG