በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የ2002ቱ አጠቃላይ ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ አልነበረም፤ በበርካታ ችግሮች የተሞላም ነበር፤ ሲል ኢዴፓ አስታወቀ


ከህግ ውጭ ከአንድ በላይ የኢህአዴግ ወኪል ታዛቢ በየምርጫ ጣቢያዎች ተመድቦ እንደነበር ይላል ኢዴፓ

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ 547 መቀመጮች ካሉት የአገሪቱ ፓርላማ ከ99.6 በመቶ በላይ የሚሆነውን ማሸነፉ ከተነገረ በኋላ ተቃዋሚዎች ውጤቱን አስመልክቶ ያላቸውን አስተያየት በመግለጫዎች ጭምር እያስታወቁ ነው።

በሸንጎው ወንበሮች ባያሸንፉም የተሻለ ድምፅ ማግኘታቸው ከተነገረላቸው ሁለት ዋነኛ ተቃቃሚዎች አንዱ የሆነው ኢዴፓም በዛሬው ዕለት በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ አቋሙን ይፋ አድርጓል።

የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ልደቱ አያሌው፥ ዋና ፀሃፊው አቶ ሙሼ ሰሙና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው አቶ መስፍን መንግስቱ በተገኙበት ኢዴፓ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጋዜጠኞች በሠጠው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫው፤ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ፥ ገዢው ኢህአዴግ የፈፀማቸው ስህተቶችና ድክመቶች ዋነኞቹ መንስኤዎች ናቸው፤ ብሏል።

«መራጮች አስቀድሞ በተወሰነላቸው ሠዓት፥ በአምስት ሠው ተቧድነውና ማንን መምረጥ እንዳለባቸው አለቃ ተመድቦ በጫና እንዲመርጡ መደረጋቸው፤ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎችም ቀድሞ ከተመዘገበው በላይ ድምፅ የተሰጠበት ሁኔታ መከሰቱ፤» በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ከተፈፀሙ የህዝብን የመምረጥ መብት ከሚጋፉ ሁኔታዎች ውስጥ መሆናቸውን ኢዴፓ ገልጧል።

«በአንዳንድ አካባቢዎች ከህግ ውጭ ከአንድ በላይ የኢህአዴግ ወኪል ታዛቢ በየምርጫ ጣቢያዎች እንዲመደብ መደረጉና በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎችም የተቃዋሚ የምርጫ ታዛቢዎች ያለ አግባብ እንዲባረረሩ መደረጉ፤ ከእንከኖቹ ጥቂቶቹ ናቸው፤» ሲል ኢዴፓ አመልክቷል።

የገዢው ፓርቲ ድክመቶችና ስህተቶች ያላቸውን በአሃዝ ሠላሳ አንድ ያደረሳቸውን ነጥቦች የዘረዘረው ኢዴፓ በችግሮቹ ስፋትና ተቋማዊ ይዘት ምክኒያት ድጋሚ ምርጫ መፍትሄ አያመጣም ሲል ይልቁን ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ድርድር በተቋማቱ ላይ እንዲጀመር ጠይቋል።

XS
SM
MD
LG