በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ወደ ዶሎ ኦዶ የሚገባው ስደተኛ ጨምሯል


ኤምኤስኤፍ ለሶማሊያዊያኑ ሕፃናት የኩፍኝ ክትባት ይሰጣል
ኤምኤስኤፍ ለሶማሊያዊያኑ ሕፃናት የኩፍኝ ክትባት ይሰጣል

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሶማሊያ ስደተኞች አሁንም ወደ ዶሎ አዶ እየገቡ ነው፡፡

ሆኖም አዲስ የሚገቡት ከስድስት ሣምንታት በፊት ከነበረው በምግብ እጦት የመመናመን ሁኔታ የተሻለ ገፅታ ይታይባቸዋል ተብሏል።

ማክሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በፊት ዶሎ አዶ የገባው ፒተር ሃይንላይን የአይሮፕላን በረራው ሜዳና ሸንተረሩን ለመቃኘትና የድርቁን ሁኔታ ከስድስት ሣምንታት በፊት ካየው ጋር ለማነፃፀር አስችሎታል። እናም በዶሎ ኦዶና አካባቢው በተከታታይ ዝናብ ሲጥል ስለነበር በአሁኑ ሰዓት ነዋሪዎቹን ከተረጂነት ባያላቅቅም ሁኔታው ተስፋ ሰጭ ነው፡፡

ምናልባትም ከሦስትና ከአራት ወራት በኋላ ህዝቡ ምርት መሰብሰብ እስከሚችል እርዳታው መቀጠል እንደሚኖርበት ሁኔታዎች ይጠቁማሉ ብሏል። የሆነ ሆኖ ከሶማሊያ ወደ ዶሎ ኦዶ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ግን አሁንም ከፍተኛ ነው በትላንትናው ዕለት ብቻ 500 ስደተኞች ከሶማሊያ ዶሎ ኦዶ ገብተዋል፡፡

የረሃብ ቸነፈር ካጠቃው ሶማሊያ ወዲህ ወደ ዶሎ ኦዶ ሲገቡ የሚቀበሏቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አዲስ የሚገቡ ስደተኞች እንደቀድሞዎቹ እጅግ የተጎዱ እንዳልሆኑ የነገሩት መሆኑን ፒተር አመልክቷል፡፡

በዶሎ አዶ ካምፕ ከስድስት ሣምንታት በፊት የነበረው ዝግጅት የጎደለው የሚመስል ሁኔታም ተለውጦ ስደተኞቹ የተሻለ አቀባበል እየተደረገላቸው መሆኑን ፒተር ጠቁሟል።

አዲስ የሚገቡት ስደተኞች ምግብ በማግኘት የተሻለ ገፅታ የሚታይባቸው ከሆነ አሁን ለመሸሽ የሚገደዱት በጦርነቱ ምክንያት ይሆን? ስደተኞቹ ገብተው ሲመዘገቡ እኛ የጠየቅናቸው ይህንኑ ነው ይላል ፒተር። ብዙዎቹ ማን ከማን ጋር እንደሚዋጋ ባያውቁም በጣም ብዙ ውጊያ እንደሚካሄድና ከዚያ የሚሸሹ መሆኑን ነው ስደተኞቹ የሚናገሩት። ስለዚህ ዕቃቸውን ጠቅልለው ለመንጎድ የተገደዱት ስላም በማጣት ነው።

የዘጠኝ ወር ነፍጡር ሆና ከአደገኛ አድካሚና ረጅም ጉዞ በኋላ ዶሎ ኦዶ በገባች በሦስት ቀናት ውስጥ የተገላገለችና ልጅዋን በስደተኝነት ስታስመዘግብ የነበረች ሴት ማነጋገሩን ፒተር ገልጿል።

"ለምንድን ነው ለመውለድ የደረሰች የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር ሆና ቤትዋን ጥላ ወደ ኢትዮጵያ ለመሰደድ የወሰነችው? እየተባባሰ የሄደው ውጊያ ነው ያሸሻት፡፡ ሰላም ማጣት ነው ከባዱን ጉዞ እንድትጀምር ያስገደዳት። የኬንያ ኃይሎችና የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች በአካባቢው ከአልሸባብ ነውጠኞች ጋር ውጊያ እንደሚያካሄዱ ይታወቃል። ከዚህ ውጊያ ለመሸሽ መሆን አለበት ከጥቂት ማምንታት ወዲህ በቀን ወደ እስከ 75 ወርዶ የነበረው የስደተኞች ቁጥር አሁን እስከ 500 የደረሰው።" ብሏል ፒተር፡፡

በዚህም ምክንያት እስከ አሥር ሺህ ስደተኞችን ማሥፈር የሚችል አምስተኛ ካምፕ በቅርቡ በዶሎ ኦዶ እንደሚከፈትና የካምፑ የሰብአዊ አገልግሎት ሠራተኞች ቁጥሩ የባሰ ይጨምራል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጿል ፒተር። ከዚያ በተረፈ ግን የእርዳታ አሰጣጡ ካሁን ቀደም ካየው የተሻለ መሆኑን ጠቁሟል።

ከስድስት ሣምንታት በፊት ከነበረው ሁኔታዎች ተሻሽለዋል። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተሻለ ፍጥነት ስደተኞቹን ሲረዱ ያታያል፡፡ ለምሳሌ ካሁን በፊት ያነጋገርኩት "ዓለም አቀፍ ልማትና ተራድዖ" የሚባል መሠረቱ ዋሽንግተን ዲሲ የሆነ ድርጅት በፊት በጣም ከባድ የነበረውን የውኃ አቅርቦት ችግር ቀርፏል። ስደተኞቹ የተሻለ ህይወት ይኖራቸዋል፡፡ በጣም አዎንታዊ የሆነ እርምጃ አያለሁ" ይላል ፒተር፡፡

አብዛኞቹ ስደተኞች በተለይም ህጻናት በተመታጠነ ምግብ እጦት የጠወለጉና ታሚዎች ስለሆኑ በካምፑ ውስጥ የህክምና እርዳታ እንደሚደግላቸው እንደ ሜድሳን ሳን ፍሮንቲዬ (ድንበር የሌሽ ሐኪሞች)ና ሴቭ ዘ ቺልድረን የተባለው ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅት በዚህ ይህን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልፆልናል ፒተር።

በመጨረሻም የዶሎ ኦዶ ካምፕ የሚገኘው በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በመሆኑ የዚያ ክልል ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችም የድርቅ ተጠቂዎች እንደመሆናቸው በካምፑ እርዳታ የማግኘት ዕድል ይኖራቸው እንደሆነ ፒተርን ሲናገር በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ያሉ በተለይም የሽምቅ ውጊያ ከሚካሄድበት አካባቢ የመጡ በካምፑ መጠለያ እንዲያገኙ የኢትዮጵያ ስደተኞች ድርጅት እንደማይፈቅድ አመልክቷል፡፡

"በቅርቡ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ የኢትዮጵያ ሶማሌዎች ስደተኞች ነን በማለት ወደ ካምፑ መጥተው እንደነበርና የኢትዮጵያ የስደተኞች ድርጅት ማንነታቸውን መርምሮ የኢትዮጵያ ዜጎች መሆናቸውን እንደተረዳና ስለዚህም በካምፑ መጠለል እንደማይችሉ እንደተነገራቸው ተነግሮኛል። ለማንኛውም እነዚህ ዜጎች እንደ ተቀሩት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ሁሉ ሌላ የእርዳታ መቀበያ መንገድ ተዘርግቶላቸዋል" ብሏል፡፡

ዘጋቢአችን ፒተር ሃይንላይን የዶሎ ኦዶ ቆይታውን ቀጥሏል፡፡

XS
SM
MD
LG