በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ መንግስት በአራት ክልሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በሰፈራ ማዛወር ጀመረ


የአፋር አርብቶ አደሮች
የአፋር አርብቶ አደሮች

የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ አሰምተዋል

በምስራቅ ሶማሊ ክልል ወደ 150ሽህ ሰዎች “ለም መሬት” ወዳለበት አካባቢ ተዛውረዋል ሲል የፌደራል ጉዳዮች ምንስቴር አስታውቋል።

የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ሽፈራው ተክለማርያም ለብሉምበርግ የዜና አገልግሎት በሰጡት ቃል መንግስት በነዚህ ክልሎች የሚኖሩ ሰዎችን ኑሮ “ለማሻሻል” ይፈልጋል ብለዋል።

በዚህም መሰረት በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሶስት አመት በሚፈጀው የሰፈራ መርሃ-ግብር ከእያንዳንዳቸው ወደ 45ሽህ የሚጠጉ አባዎራዎችን በሰፈራ ያዛውራል።

በአፋርና ሶማሊ ክልል ደግሞ ሰፈራው በአንድ አመት ወስጥ ተፈጻሚ ሲሆን፤ በሶማሊ ክልል ወደ 350ሽህ ሰዎች በአፋር ደግሞ ከ50ሽህ እስከ 80ሽህ ሰዎች እንደሚሰፍሩ ሚኒስትሩ ሽፈራው ተክለማርያም ለብሉምበርግ ገልጸዋል።

በጋምቤላ አካባቢ በተለይ 3/4ኝኛ የሚሆነው የክልሉ ህዝብ ወደ አዲስ ቦታ ይሰፍራል። አንድ ማንጎ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለቪኦኤ ሲናገሩ በጋምቤላ የሚደረገውን ልማት እንደሚደግፉ ገልጸው፤ ከተወለዱበት ቀየ ለም መሬታቸውን ትተው ተፈናቅለው፤ በምትኩ የተሰጣቸው መሬት ጭንጫና ድንጋያማ እንደሆነ ይናገራሉ።

“ከነበርንበት ለም ቦታ ተነስተን ወደ ደረቅ ቦታ አዘዋውረው፤ ይዞታችንን ለባለሃብት እየሰጡ ነው” ብለዋል በግብርና ስራ የተሰማሩት አቶ ማንጎ።

የአካባቢው ማህበረሰብ ልማቱን ይፈልገዋል ያሉት አቶ ማንጎ፤ ልማቱ ማህበረሰቡን ያሳተፈና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረገ እንዲሆን መታቀድ ነበረበት ብለዋል።

“ክሊኒክ የሌለበት፣ ውሃ የሌለበት፣ ትምህርት ቤት የሌለበት ቦታ እንዴት ስፈሩ እንባላለን?” ሲሉ ጠይቀዋል።

በጋምቤላ ክልል ወስጥ አብዛሃኛው መንደሮችና ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ሀገር እንዲለቁ እየተገደዱ ነው። እምቢ የሚሉትን በአፈሙዝ ማስገደድም ተጀምሯል ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች።

የጋር እንቅስቃሴ ለአዲሱቷ ኢትዮጵያ የሚባል ቡድን የሚመሩት ኦባንግ ሜቶ የጋምቤላ ተወላጅ ናቸው። በክልሉ ልማት መኖሩ “እሰየው” የሚባል ሆኖ ሳለ፤ ማህበረሰቡን እንዲህ በሃይል ማፈናቀል ግን፤ ከዜጎች መብት ጥሰት ይቆጠራል ብለዋል።

“ይሄ ልማት የሚባለው መንግስቱን ይጠቅም ካልሆነ በስተቀር የጋምቤላን ህዝብ የሚጠቅም አይደለም” ይላሉ አቶ ኦባንግ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተወላጅ የሆኑት ኢብራሂም ዩሴፍ በቤኒሻንጉልም የሚታየው ከጋምቤላ የተለየ አይደለም ይላሉ። “ወያኔ (የኢህአዴግ አስተዳድር) የሀገሬው ሰዎች ከመሬቱ እንዲወጡ ታስቦ ነው” ብለዋል።

በሶማሊ ክልል ነፍጥ አንስቶ የሚዋጋው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ሶማሊያዊያንን ወደ ጅጅጋና ሌሎች አካባቢዎች እያዛወረ “የህዝብ ማጎሪያ ጣቢያ” ባላቸው ስፍራ እያቆየ ነው ብሏል።

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ሽፈራው ተክለማርያም ለብሉምበርግ ሲናገሩ፤ በተለይ በሶማሊያ ክልል የሰፈራው ስራ በክልሉ የሚታየውን የጸጥታ ችግር በማሰብ አለመከናወኑን ተናግረዋል።

“በረጅም ጊዜ ሊረዳ ይችላል፤ አሁን ግን አላማው እነዚህ ዜጎች ሀገሪቱ ከምታሳየው ከ11-15 ከመቶ እድገት በመጭዎቹ አምስት አመታት ተቋዳሽ እንዲሆኑ ነው” ብለዋል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG