በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አምነስቲ በኢትዮጵያ የተቃዋሚ መሪዎች የታሠሩት እኔን ስላናገሩ ነው ይላል


ሰሞኑን በቁጥጥር ሥር የዋሉት የኦሮሞ ተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎች የታሠሩት ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰዎች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ መሆኑን የቡድኑ የኢትዮጵያ ተመራማሪ ክሌር ቤስተን ገለፁ፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ተቋማቸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ውስጥ አለ የሚባለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የግልፅነት ጉዳይ ለመፈተሽ ፍቃድ ጠይቆ በአምስት ወሩ ማግኘቱንና ቡድኑ ካለፈው ነሐሴ 11 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ለ12 ቀናት መቆየቱን የአምነስቲ የኢትዮጵያ ተመራማሪ ክሌር ቤስተን ተናግረዋል፡፡

እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኦሮሞ ተወላጆች መታሠራቸውን መስማታቸውን የገለፁት ክሌር የተጨበጠ ቁጥር ገና በእጃቸው እንደሌለ ተናግረው ይሁን እንጂ ለጊዜው ያሰባሰቧቸው መረጃዎች ተካሄዱ የተባሉትን እሥሮች የተወሰኑ ቁጥሮች እንደሚጠቁሙ አመልክተዋል፡፡

በዚህ ዓመት በመጋቢትና በሚያዝያ መካከል ሁለት ወይም ሦስት መቶ የሚሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች እንደታሠሩ እናውቃለን የሚሉት ቤስተን "ከዚያም ወዲህ በርከት ያሉ ሰዎች ታስረዋል" ብለዋል፡፡

ባለፈው ቅዳሜም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሁለቱ ተቃዋሚ መሪዎች ከመያዛቸው ከጥቂት ቀናት በፊት ሁለቱም ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋር ተነጋግረው እንደነበር ሚስ ቤስተን አስታውሰው ኦልባና ሌሊሣን ከመታሠራቸው ከአንድ ቀን በፊት፣ ሌላኛውን ታሣሪ በቀለ ገርባን ደግሞ ከመታሠራቸው ከአራት ቀናት በፊት ያገኟቸው መሆኑን፣ ከቢሯቸው ሲወጡም የደኅንነት ሰዎች ፎቶግራፍ ያነሷቸው እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ክሌር ቤስቲን አክለውም በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ተጠርተው በአፋጣኝ ከሃገር እንዲወጡ የተነገራቸው መሆኑንና ለመውጣት መገደዳቸውን ገልፀዋል፡፡

የቡድኑን አባላት ባነጋገሩ በኋላ የሁለቱ ተቃዋማ ፓርቲዎች መሪዎች መታሠር በእጅጉ ያሣሰባቸው መሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የአቶ በቀለ ገርባና ኦልባና ሌሊሣን መታሠር አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ሽመልስ ከማል አንደኛው የታሠሩት በቅርቡ በሽብር ፈጠራ ምክንያት ከታገደው ኦነግ ጋር አላቸው በተባለ ግንኙነት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG