በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሲፒጄ ትግራይ ውስጥ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ጠይቀ


የፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ጋዜጠኛ የትርጉም ረዳት ፍጹም ብርሃነ እና የፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ ሪፖርተር ተርጓሚ አሉላ አካሉ መቀሌ ውስጥ በኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች በቁጥጥር መዋላቸው ተገለጸ።

ፍጹም ብርሃነ ባለፈው ዐርብ አሉላ አካሉ ደግሞ ቅዳሜ መያዛቸውን ነው ዜናው ያመለከተው። የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች እና ሪፖርተሮች ወደክልሉ ገብተው እንዲዘግቡ መፍቀዱ ሲታወስ የዜና ተቋማቱም ይህንኑ ተከትሎ ጋዜጠኞቻቸውን መላክ ጀምረዋል።

በትናንትናው ዕለት ደግሞ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ግርማይ ገብሩ እና ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የሚሰራው ታምራት የማነ ቅዳሜ ጠዋት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ምንጮች ለቪኦኤ ገልጸዋል። ስለጋዜጠኞቹ መታሰር ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽንስ ቢሮ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለጋዜጠኞች ደህንነት የሚሟገተው ቡድን /ሲፒጄ/ የኢትዮጵያ መንግሥት የታሰሩትን ጋዜጠኞች እና ሌሎችም የሚዲያ ሰራተኞች እንዲለቀቅ ጠይቋል።

ቢሮው ኒው ዮርክ የሆነው ሲፒጄ በቅርቡ በትግራይ ክልል ግጭቶችን የተመለከተ ዘገባ ለማጠናቀር በመሞከራቸው ቢያንስ አራት ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሰራተኞች መያዛቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስን እና ዘ ፋይናንሽያል ታይምስ ጋዜጣን እንዲሁም ስማቸው ያልተገለጸ ሁለት ጋዜጠኞችን ጠቅሶ አመልክቷል።

ትናንት ሰኞ መቀሌ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛው በዚያ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ እስር ላይ መሆኑን ቢቢሲ አስታውቋል።

የሲፒጄ የአፍሪካ ተጠሪ ሙቶኪ ሙሞ ባወጡት መግለጫ "በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ በነጻነት ተጠናቅሮ የሚቀርብ ዘገባ ዕጥረቱ አስቀድሞም በጥልቅ ሲያሳስበን የቆየ ጉዳይ ነው ካሉ በኋላ፤አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ የጦር ኃይል ጋዜጠኞችንና እና ሌሎችንም የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች ማሰሩ ፍራቻ እና ራስን በራስ በሳንሱር ወደመገደብ ማምራቱ የማይቀር ነው" ብለዋል።

XS
SM
MD
LG