የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፣ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ድኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በዋስ እንዲለቀቁ በየነ። የተከሳሹ ባለቤት ወይዘሮ ስንታየሁ አለማየሁ፣ አቶ ታዬ በ20 ሺሕ ብር ማስያዣ ወይም በሰው ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ መወሰኑን ተናግረዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዛሬ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት፣ ሕግ ህገወጥ የጦር መሳርያ ይዞ ‘በመገኘት’ በሚል ለቀረበባቸው ክስ በእስር ላይ ኾነው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ያሉ አቶ ታዬ ደንደአ ከእስር እንዲፈቱ ወስኗል።
የአቶ ታዬ ባለቤት ወይዘሮ ስንይታየሁ አለማየሁ፣ ሰበር ሰሚ ችሎት አቶ ታዬ የ20ሺሕ ብር የዋስትና ገንዘብ አስይዘው ወይም የሰው ዋስ አቅርበዉ እንዲለቀቁ መወሰኑን ተናግረዋል። አክለውም፣"ጉዳያቸዉን የተመለከቱትም አምስት የፍርድ ቤቱ ዳኞች ናቸዉ፣ እስካሁን አልተለቀቀም፣ የመውጫ ደብዳቤ እያጻፍን እንገኛለን" ብለውናል።
አቶ ታዬ ከዚህ በፊት በፌደራል ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዋስ መብት ጥያቄያቸዉ ውድቅ ተደርጎ እንደነበረ ይታወሳል።
ከታኅሳስ 1 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ደ’ኤታ ጉዳያቸው እየታየ በሚገኝበት፣ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሕገ-መንግስትና ሕገ-መንግሥት ሥርዓት ችሎት፣ የተከሳሹን ቀሪ የመከላከያ ምስክሮችን በማሰማት ላይ ናቸው።
ከስድስት ቀናት በፊት ኅዳር 17፣ 2017 ዓ.ም. ለቀሪ መከላከያ ምስክሮቹ መጥሪያ እንዲጻፍ አዞ፣ ለታኅሳስ 3/2017 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶአል። አቶ ታዬ ፍርድ ቤት የሚቀርቡት ያለ ጠበቃ ሲኾን፣ ይም የኾነው ሊቀጥሯቸው በሚችሉ ጠበቆች ላይ ማስፈራሪያ በመድረሱ ምክኒያት ነው፣ ሲሉ አቤቱታ ማቅረባቸው ይታወሳሉ። ፍርድ ቤቱ በዚኽና በሌሎች በተከሳሹ በቀረቡ የመብት ጥሰት አቤቱታዎች ላይ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አጣርቶ የሚያመጣው ሪፖርት ለመጠባበቅ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
መድረክ / ፎረም