በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ አንድ ትሪሊየን ብር የሚጠጋ በጀት አቀረበ


የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት
የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት

የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ዛሬ ዐርብ፣ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሔደው መደበኛ ስብሰባ፣ የቀጣዩ የ2017 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት በጀት፣ ወደ አንድ ትሪሊየን የሚጠጋ ብር እንዲኾን በአዘጋጀው የዐዋጅ ረቂቅ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ በመወሰን፣ ይጸድቅ ዘንድ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፏል።

ለምክር ቤቱ የቀረበው የ2017 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት የበጀት ዐዋጅ ረቂቅ፡- የፌደራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎችን፣ የካፒታል ወጪዎችን፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍን፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የሚውል ድጋፍንና ተጠባባቂ ወጪን እንደሚያካትት ተገልጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው፥ የ2016 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥትን የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም መነሻ በማድረግና የመንግሥት የፋይናንስ ዐቅምንና ተጠባቂ ገቢዎችን ታሳቢ በማድረግ እንደኾነ አብራርቷል።

መግለጫው አክሎ፣ “የ2017 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት በጀት፥ የዐሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል በኾነው የ2016-2018 የልማት እና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን እና የ2017-2021 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፊስካል ማኅቀፍን ማስፈጸም እንዲቻል በሚያደርግ መልኩ” መዘጋጀቱንም አመልክቷል።

ምክር ቤቱ፣ በዛሬው 34ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ ከፌደራል መንግሥት በጀት በተጨማሪ፣ የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያ እና አስተዳደሩን ለመወሰን በወጣ የዐዋጅ ረቂቅም ላይ መወያየቱን እና ወደ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ማሳለፉ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።

ፈንድ ማቋቋሚያው የዐዋጅ ረቂቅ የተዘጋጀው፣ “የአረንጓዴ አሻራ ልማት በተቀናጀ እና ተገቢውን ሀብት መመደብ በሚያስችል የፋይናንስ አሠራር ሥርዐት መደገፍ ያለው አስፈላጊነት ስለታመነበት መኾኑን” በመግለጫው ላይ አክሎ አመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG