በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጦርነቱ እንዲቆምና ድርድር እንዲጀመር ግፊቶች ቀጥለዋል


ጦርነቱ እንዲቆምና ድርድር እንዲጀመር ግፊቶች ቀጥለዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:12 0:00

ጦርነቱ እንዲቆምና ድርድር እንዲጀመር ግፊቶች ቀጥለዋል

የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና ህወሓት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በአስቸኳይ አቁመው ወደ ድርድር እንዲገቡ ዩናይትድ ስቴትስና እንግሊዝ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ‘ሁለቱም ወገኖች’ የሚል አቀራረብን እንደማይቀበል ያሳወቀ ሲሆን ህወሓትም ተመሳሳይ አቋም እንዳለው መግለፁ አይዘነጋም።

በሌላ በኩል ተዋጊዎቹ ለጦርነቱ ዳግም መቀስቀስና መስፋፋት መወነጃጀላቸውን አሁንም ቀጥለዋል።

“የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ” አወጣው በተባለ መግለጫ ዛሬ ነኀሴ 26/2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር ከኤርትራ ጦር ጋር በመጣመር “ከሌሊቱ 10 ሰዓት ተኩል ጀምሮ በአራት አቅጣጫ ከፍተኛ ጥቃት ጀምሯል” ሲል ከስሷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ “ህወሓት ወረራውን እያስፋፋ መጮኹን ቀጥሎበታል” ብሏል። ይሁን እንጂ ህወሓት በሰሜን ምዕራብ ግንባር “ሌሊቱን ተከፈተብኝ” ስላለው አዲስ ጥቃት ከአዲስ አበባም ይሁን ከአሥመራ በቀጥታ የተሰማ ምላሽ የለም።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትና የዓለምአቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “መንግሥትም ህወሓትም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በአስቸኳይ እንዲያቆሙና ግጭቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዩናይትድ ስቴትስ ትጠይቃለች” ብለዋል።

“ጦርነቱ ዳግም መቀስቀሱና ይህም አደጋ ላይ የሚጥለው ህይወት በእጅጉ ያሳስበናል” ሲሉም አክለዋል።

ዩናይትድ ኪንግደምም እንዲሁ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ ያቀረበት ሲሆን የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ቪኪ ፎርድ ባወጡት መግለጫ “ይህንን ግጭት ለመፍታት ብቸኛው መንገድ ጦርነቱን ማቆምና በአስቸኳይ የፖለቲካ ድርድር መጀመር ነው” ብለዋል። ለዚህም ሃገራቸው የአፍሪካ ኅብረትን የሽምግልና ጥረቶች እንደምትደግፍ የገለፁት ሚኒስትር ፎርድ ግጭቱ ከመባባስ ለማስቆም ጥረቶቹ እንዲጠናከሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ “በህወሓት እየተፈፀሙ ያሉ ጥፋቶችን ለማስቆም መንግሥት ለሰላማዊ አማራጭ ያደረጋቸው ጥረቶች ሁሉ እየመከኑ ባሉበት ሁኔታ አሸባሪውን ህወሃት መጫን ሲገባቸው ‘ሁለቱም ወገኖች’ በሚል የሚወጡ መግለጫዎች ከእውነታው ያፈነገጡ በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም” ብሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ ‘ሁለቱም ወገኖች’ በሚል የሚቀርበውን ጥሪ እንደማይቀበል ያስታወቀው ህወሓትም ቢሆን ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርግ መጠየቁ ይታወቃል።

ወገኖቹ ለጦርነቱ ዳግም መቀስቀስና መስፋፋት መወነጃጀላቸውን እንደቀጠሉ ሲሆን የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ አወጣ በተባለው መግለጫ ዛሬ ነኀሴ 26/2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር ከኤርትራ ጦር ጋር በመጣመር “ከሌሊቱ 10 ሰዓት ተኩል ጀምሮ በአራት አቅጣጫ ወደ አድያቦ ከፍተኛ ጥቃት ጀምራል” ሲል ከስሷል።

ጥቃቱ ያነጣጠረው ከፊቕያ ገብረ ወደ አዳመይቲ፣ ከሰላሞ ወደ ሽራሮ፣ ከጎቦ ፅንዓት ወደ ዓዲ አሰርና ዕርዲ ማትያስ፣ ከዓዲ ጎሹ ወደ ዓዲ አሰር ማዕከል እንደሆነ መግለጫው ይናገራል። ይህንኑ መግለጫ በትዊተር ገፃቸው ያስተጋቡት የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ “ኃይሎቻችን በመከላከል ላይ ናቸው” ብለዋል።

መግለጫው ‘ጠላት’ ሲል የገለፀው ፌዴራሉ መንግሥት “ሁሉንም የሰላም አማራጮችን በመተው ያልተለመደ ግዙፍ መደበኛና ኢመደበኛ ኃይል በማሠማራትና ከውጭ ኃይል ጋር በመተባበር መጠነ ሰፊ ጦርነት ጀምሯል” በማለት ይከስሳል።

በሌላ በኩል “ህወሓት ወረራውን እያስፋፋ መጮኹን ቀጥሎበታል” የሚለው የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ “ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ገፍቶ በየአቅጣጫው በለኮሰውና ዛሬም እያስፋፋ ባለው እሳት ንፁሃን እየተገደሉ ነው፤ ሕዝብ እየተፈናቀለ፣ ንብረትም እየወደመ ነው” ሲል አመልክቷል።

መግለጫው በመቀጠል “ህወሓት ተደጋጋሚ የሰላም አማራጮችን በመግፋት የከፈተው” ያለውን ጥቃት በመከላከል ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል።

የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሆን ውጊያ ከፍቷል በሚል ከህወሓት ለቀረበው ክስ ግን የኢትዮጵያ መንግሥትም ይሁን የኤርትራ መንግሥት እስከአሁን በቀጥታ የሰጡት ምላሽ የለም።

ይሁን እንጂ በኬንያ የኤርትራ አምባሳደር በየነ ርዕሶም ዛሬ ባወጡት በህወሓት ላይ ወቀሳ ያዘለ ትዊት “ህወሃት ... ተጨማሪ ስህተቶችን እንዲሠራ ሌላ ዕድል አያገኝም፤ ይልቅ እንዲቆም ይደረጋል። የኤርትራ መከላከያ ኃይሎች ያሸንፋሉ” ብለዋል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ትናንት ባወጡት ትዊት ህወሓትን “በኤርትራ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ለመፈፀም እያሰበ ነው” ሲሉ ከስሰዋል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴ’ኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆነ ዲፕሎማቶችና የዓለምአቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በሃገሪቱ የወቅቱ ሁኔታ ላይ ዛሬ፤ ሐሙስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህወሓት ተፈፅሟል ያሉትን መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማስቆም ፌዴራል መንግሥቱ የሚያደርገውን ጥረት የሚደግፉ ሃገሮች አመስግነው በአንፃሩ ደግሞ ህወሓትን የሚደግፉ መኖራቸውን መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገፁ ላይ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በህወሓት ላይ በሚወስደው እርምጃ ሲቪሎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑንና ከወታደራዊ ዒላማዎች እንዲርቁም ያለማቋረጥ ማስጠንቀቂያ እየሰጠ መሆኑን መግለፃቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ ባለፈው ዓርብ ‘መቀሌ ላይ ተፈፅሟል’ በተባለ ጥቃት ሁለት ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸው ቢገለፅም የኢትዮጵያ መንግሥት አስተባብሏል።

ያም ሆነ ይህ የጦርነቱ ማገርሸት ሰብዓዊ ችግሮችን እያባባሰ መሆኑን የተለያዩ ዓለምአቀፍ አካላት እየገለፁ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሠፈሩት ፅሁፍ “በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልሎች የሰብአዊ እርዳታ ሠራተኞች እሥራት፣ የነዳጅ ዘረፋና የተሸከርካሪ ቅሚያን ጨምሮ ተቀባይነት የሌለው ማስተጓጎል እየደረሰባቸው ነው” ብለዋል።

ዕርዳታ ለተቸገሩት ይደርስ ዘንድ ሁሉም ወገኖች ሰብዓዊ ተግባራትን እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር በበኩላቸው “በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ እንደገና ሲቀሰቀስና የእርዳታ አቅርቦት ሲቋረጥ የአፍሪካ መንግሥታትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ እርዳታና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዳይደርሱ ማስተጓጎልን እንደ ጦርነት ስትራቴጂ ተጠቅሞ እንዳይቀጥልና ማዕቀብ እንደሚያስጥል ግልፅ ማድረግ አለባቸው” ብለዋል።

ይሁን እንጂ አቶ ደመቀ መኮንን ዛሬ ለዲፕሎማቶቹ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ሰብዓዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ተኩሱ በሰብዓዊ ምክንያት መቆሙን ተከትሎ ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ዜጎችን “ካሉበት አስከፊ ሁኔታ ለማውጣት የተደረገውን አበረታች ጥረት” ማድነቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ይናገራል።

ነገር ግን የዓለም የጤና ድርጅት ኃላፊን ጨምሮ አንዳንድ አካላት ከተሰጣቸው ኃላፊነት አልፈው በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና እንደሚያደርጉ መግለፃቸውንም አንስቷል።

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደምም “አንዳንድ የዓለምአቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞችና ኃላፊዎች ከህወሓት ጋር በመወገን ጫና ሊያሳድሩብኝ ይጥራሉ” ሲል በተደጋጋሚ መክሰሱ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ተቋማቱና ክስ የሚቀርብባቸው ግለሰቦች በተደጋጋሚ ሲያስተባብሉ ይደመጣል። ህወሓትም ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚቀርበውን ውንጀላ አይቀበልም፡፡

እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሆነ ግጭቶች እየተባባሱ ባሉበት በአሁኑ ወቅትም ቢሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላምን ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኑን አቶ ደመቀ ገልፀዋል። በውይይቱ ላይ ከዲፕሎማቶች ወገን ስለተነሳው ሃሳብ የሚኒስቴሩ መግለጫ ያለው ነገር የለም።

/ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/

XS
SM
MD
LG