የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን የአፍሪቃ አገሮች ከሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ጋር ግንኙነት አቋርጠው ከተቃዋሚዎቹ ጋር እንዲሠሩ ጠየቁ ።
ክሊንተን ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በአፍሪቃ ኅብረት ማዕከል ባደረጉት ንግግር ነው ሃሣቡን ያቀረቡት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የአፍሪቃ መሪዎች ሚስተር ጋዳፊ የተኩስ አቁም ተቀብለው ሥልጣን እንዲለቅቁ እንዲጠይቁም ሃሳብ አቅርበዋል። በተጨማሪም የጋዳፊን ዲፕሎማቶች ከአገሮቻቸው አባርረው የሊቢያን ሸማቂዎች ብሔራዊ የሽግግር ሸንጎ እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሊንተን ጋዳፊ ለረጅም ዓመታት የአፍሪቃን ተቋማት መርዳታቸውን ጠቅሰው ነገር ግን ሥልጣን የመልቀቃቸው ጊዜ በጣም አልፎበታል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በአራት የአፍሪቃ አገሮች ባደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ የመጨረሻዋ ናት፤ ጉዟቸውን የጀመሩት ባለፈው ሣምንት በአረብ ኤምሬቶች ሲሆን እዚያም ኢጣሊያና ፈረንሣይ እንዲሁም ሌሎች አገሮች ለሊቢያ አማፂያን የ1.1 ቢሊዩን ዶላር እርዳታ ሊሰጡ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም።
ሚስ ክሊንተን ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር ተነጋግረዋል።
ወደ መጨረሻ ላይ በደረሰን ዜና ግን ኤርትራ ውስጥ የፈነዳው እሣተ ገሞራ ባሠራጨው የአመድ ብናኝ ምክንያት ሚስ ክሊንተን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እየተመለሱ መሆናቸው ታውቋል።
ለዝርዝር ዘገባዎች በቀጥታ የተላለፉትን የሪፖርተሮቻችንን ዘገባዎች ያዳምጡ፡፡