በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አቶ ምግባሩ ከበደና ጀነራል አሳምነው ፅጌ ህይወታቸው አለፈ


አቶ ምግባሩ ከበደና ጀነራል አሳምነው ፅጌ
አቶ ምግባሩ ከበደና ጀነራል አሳምነው ፅጌ

ጀነራል አሳምነው ፅጌ መገደላቸው ተገለፀ፣ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደም በሕክምና ላይ እያሉ ሕይወታቸው ማለፉ ታወቀ።

በአማራ ክልል የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩት ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ፤ "ዘንዘልማ" በሚባልና ጎንደር መውጫ አካባቢ በሚገኝ ቦታ በተኩስ ልውውጥ መገደላቸውን፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ለአሜሪካ ድምፅ ገለፁ። በተጨማሪም፣ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆፒታል ሕክምና ላይ እንዳሉ ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።

ባለፈው ቅዳሜ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ቢሮ በነበረው የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ በተካሄደ ተኩስ፣ ርዕሰ-መስተዳድሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን እና የርዕሰ መስተዳድሩ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ መገደላቸው ይታወሳል።

ቅዳሜ ከሰዓታት በኋላ፣ አዲሳባ ውስጥ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ኤታ ሞዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን፣ ከቀድሞ የጦር አዛዥ ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ ጋር በመኖሪያ ቤታቸው እንዳሉ በጠባቂያቸው መገደላቸው ይታወቃል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት፣ የሁለቱ ግድያ የተያያዘ ነው።

የጥቃቱ ዋና ምክንያት ግልጽ አይደለም። ተንታኞች እንደሚናገሩት ግን፣ ብሔርተኛ አማራ የነበሩት ሜጀር ጀነራል አሳምነው፣ ሚሊሽያ ለማቋቋም ጥረት በማድረጋቸው፣ ከሥራቸው ሊባረሩ እንደሚችሉ ሥጋት ነበራቸው።

እአአ በ2009 በተካሄደ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ፣ ባለፈው ዓመት ነው በዶ/ር ዐቢይ አመራር የተለቀቁት።

አንዳንድ ያልተረጋገጡ ምንጮች ጀነራል ሰዓረንና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራን ገድሏል የተባለው ጠባቂ እራሱን እንዳጠፋ ይናገራሉ።

አዲሳባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምበሲ በበኩሉ፣ ባለፈው ቅዳሜ ባሕር ዳር ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት አሳዛኝና አስደንጋጭ መሆኑን አስታውቋል። "በሟቾቹ ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ ባገለገሏት ኢትዮጵያና በተቋማቱ ላይ እንደተፈፀመ የሚቆጠር ነው" ብሏል ኤምበሲው።

ኢትዮጵያ በምታካሂደው ፖለቲካዊና ኤክኖሚያዊ ለውጥ ለምትፈልገው ዕርዳታ ሁሉ ዩናይትድ ስቴትስ በተጠንቀቅ ላይ መሆኗንም፣ ኤምበሲው ትናንት ዕሑድ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቲቦር ናጅ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የቅዳሜው ጥቃት ምናልባት በዶክተር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት ያልተደሰቱና፣ እየወሰዱ ያሉት ፈጣን ለውጥም ያልተመቻቸው ያቀነባበሩት ነው ብለዋል።

የቀድሞው ገዢ መደብ ርዝራዦች ሥልጣን ላይ መኖራቸውን ያመለከቱት፣ በኢትዮጵያ የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደት ቲቦር ናጅ አክለውም፣ ዶ/ር ዐቢይ ብዙ ሊያከናውኗቸውና ከግብ ሊያደርሷቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የኤርትራ መንግሥትም፣ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ባስተላለፈው መልዕክት፣ በከሸፈው መፈንቅለ-መንግሥት ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡት ለአማራ ክልል ፕሬዚዳንት፣ ለረዳቶቻቸው፣ ለኢትዮጵያው ኤታ ማዦር ሹምና በጡረታ ላይ ለነበሩት ሜጀር ጀነራል ገዛኢ ጥልቅ ኃዘኑን ገልጿል።

በተያያዘ ዜና፣ በተባለው መፈንቅለ-መንግሥት መነሾ ሕይወታቸውን ላጡ ባለሥልጣናት ክብር፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ በግማሽ ሰንደቅ እየተውለበለበ ሲሆን ዛሬ ሰኞ ብሔራዊ የኃዘን ቀን እንዲሆን መወሰኑም ታውቋል።

በመፈንቅ መንግሥቱ ሕይወታቸን ያጡ ባለሥልጣናት የአስከሬን ሽኝትና የቀብር ሥነ-ሥርዓትም፤ ፕሮግራም የተያዘለት መሆኑ፣ ታውቋል። በዚሁ መሠረት፣ የጀነራል ሰዓረ መኮንን እና የሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ አስከሬን ነገ ማክሰኞ በሚሌኒየም አዳራሽ ሽኝት ከተደረገለት በኋላ ቀብራቸው መቀሌ ውስጥ እንድሚፈጸም ታውቋል።

የአማራ ክልል ፕሬዚደንት የዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የረዳቶቻቸው የአቶ እዘዝ ዋሴና የአቶ ምግባሩ ከበደ የቀብር ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸመው ባሕር ዳር ሲሆን፣ የሦስት ቀን ኃዘን እንደሚደረግም ታውቋል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG