ታላቋ የበጎ አድራጎት ተምሳሌት አበበች ጎበና ከዚህ አለም በሞት ተለዩ
በቅርቡ በኮሮና በሽታ ምክንያት በጳውሎስ ሆሰፒታል በጽኑ ህሙማን ክፍል ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ጠዋት በተወለዱ በ85 ዓመታቸው ማረፋቸውን ከበጎ አድራጎት ተቋማቸው የህጻናት ክብካቤ እና ልማት ማህበር የወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በ1928 ዓምበሰሜን ሸዋ በግራር ጃርሶ ወረዳ በቶርበን አሼ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ሸበል አቦ በተባለች የገጠር መንደር የተወለዱት እናት አበበች ጎበና በወቅቱ በነበረው ባህልና ልማድ ገና የ11 ዓመት ልጅ እንዳሉ ትዳር እንዲይዙ ሲገደዱ ዕምቢኝ ብለው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በዚያ ከግለሰቦች ቤት ከማገልገል እስከ ምርት ክፍል ኃላፊነት እንዳገለገሉ በተቋማቸው የፌስቡክ ገጽ የወጣው የህይወት ታሪካቸው ያትታል፡፡
አብያተ ክርስትያናትን አገልጋይ የነበሩት ወይዘሮ አበበች አጋጣሚ በ1972 ዓም መንፈሳዊ ጉዞ ላይ ሳሉ በጊዜው በነበረው ድርቅ ሳቢያ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሁለት ህፃናትን በመያዝ አበበች ጐበና ህፃናት ክብካቤና ልማት ማህበርን መሰረቱ፡፡
እነሆ ከዚያ በቀጠሉት አርባ አንድ ዓመታት ብዙ መቶ ሺህ ህፃናትን ተንከባከበው ለቁም ነገር ያበቁ ሲሆን በተለያዩ ድህነት ቅነሳ ፐሮግራሞች ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ድጋፍ መስጠታቸውን ጨምሮ አውስቷል፡፡
በዚህ የላቀ በጎ ስራቸውምበተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች ታላላቅ ሽልማቶችና ዕውቅናዎችን የተቀበሉ ሲሆን የጅማ ዩኒቨርስቲ ስለሰብዐዊነታቸው የክብር ዶክትሬት ድግሪ ሰጥቷቸዋል፡፡
የታላቋን የበጎ አድራጎት ሰው ዜና ዕረፍት ተከትሎ የሃዘን መግለጫዎች በመጉረፍ ላይ ናቸው፡፡