በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢሣት ሥርጭቱን ቀጥሏል


ለስድስት ወራት ያህል ሥርጭቱን አቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ሣተላይት ቴሌቪዥን (ኢሣት) ከዓርብ፤ ኅዳር 24 ቀን ጀምሮ አገልግሎቱን መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ሥርጭቱን ለኢትዮጵያና አካባቢዋ፣ እንዲሁም ከሰሜን አሜሪካ በስተቀር በመላው ዓለም እንደሚያደርስ የገለፁት የኢሣት ቃልአቀባይ አቶ ክንፉ አሰፋ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት መግለጫ ከተመሠረተ የዘጠኝ ወራት ዕድሜ ያለው የጣቢያቸው ሥርጭት ለአራተኛ ጊዜ ለመቋረጥ ተገድዶ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

አቶ ክንፉ ሲናገሩ ፕሮግራሞቹን ተቀብሎ የማሠራጨቱን አገልግሎት ይሠጣቸው ከነበረው ከዐረብ ሣት ጋር ባደረጉት ውይይት ሥርጭቱ የተቋረጠው በተለይ በሰሜን አሜሪካ ወደ ሣተላይት በሚላክ ሞገድ ምክንያት መረበሽ መፈጠሩን ገልፀው ሞገዱ የሚላከው በኢትዮጵያ መንግሥት እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ሌሎችም ሥርጭቶች ተፅዕኖው የጎዳቸው በመሆኑ ዐረብ ሣት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ መንግሥታት፣ እንዲሁም ለኢሣት ደብዳቤ ፅፎ ሁሉንም ያወረዳቸው መሆኑን ቃልአቀባዩ ጠቁመው በኋላም ዋነኛው ዒላማ የነበረው ኢሣት እንደነበረ በመረዳት ዐረብ ሣት ሌሎች ደንበኞቼን በናንተ ምክንያት ማጣት አልፈልግም ብሎ አገልግሎቱን መስጠት እንዳቆመ አስረድተዋል፡፡

ለስድስት ወራት ያህል ከአየር ላይ የጠፉትም ሌላ የሣተላይት ሥርጭት አገልግሎት ሰጭ ሲያፈላልጉ በመቆየታቸው እንደነበር አቶ ክንፉ ገልፀዋል፡፡

"ኢሣት የተቋረጠው በራሣቸው የውስጥ ችግር ምክንያት ነው" ሲሉ በቅርቡ አንድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣን የሰጡትን መግለጫ ቃልአቀባዩ አስተባብለዋል፡፡

ከኅዳር 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ በታይኮም ሣት በ "ሲ ባንድ" ለሚተላለፈው አዲሱ ሥርጭታቸው ከአገልግሎት ሠጭው ጋር የተራዘመ ጊዜ ውል መፈረማቸውንና በውስጣቸውም ሆነ ከክፍያ ጋር የተያያዘ ችግር እንደሌለባቸው አቶ አውሮፓ የሚገኙት የኢሣት ቃል አቀባይ አቶ ክንፉ አሰፋ አመልክተዋል፡፡

ለዝርዝሩ ቃለምልልሱን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG