ዛሬ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል አባላት የሰብአዊ መብት መርማሪ ኮሚሽን ባቀረበው ዘገባ ላይ ሃሳባቸውን እየሰጡ ነው። ይህን ውሳኔ የሚቃወሙ ኤርትራውያን በጄኔቫ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሄዱ ውለዋል። እስራኤል ውስጥ ደግሞ መርማሪው ኮሚሽን ያወጣውን የሚደግፉ ኤርትራውያን ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተሰይመው ስለኤርትራ ጉዳይ ጥናት ያቀረቡት ኮሚሽነሮች ኤርትራ በፍጹማዊ አገዛዝ የምትገዛ ሃገር ናት። ከመንግስታዊ ተጽእኖ ነጻ የሆነ የፍርድ ስርአት፣ ብሄራዊ ሸንጎ ወይም ዲሞክራስያዊ ተቋማት የሏትም ይላሉ። በህዝቡ ላይ የፍርሀት ድባብ በማስፈን የፖለቲካ ተቃውሞን ለማስወገድ ሲባል የባርነት ወንጀልን፤ እስራትን፤ እንደወጡ መቅረትን የመሳሰሉት ሁኔታዎች ይፈጸማሉ ሲሉም ኮሚሽነሮቹ ጠቁመዋል።
መርማሪዎቹ አያይዘውም ጎብኚዎች በኤርትራ ላይ ላዩን በሚያዩት የአስመሳይ ሰላም መታለል የለባቸውም ብለዋል። የመርማሪው ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማይክ ስሚት ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ሲናገሩ አስመራን የሚጎበኙ ሰዎችም ሆኑ እዛ የሚኖሩ የውጭ ሃገራት ተወላጆች ለየት ያለ ገጽታ ነው የሚታያቸው ብለዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።