ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ባን-ኪሙን ቢሮ የወጣው ሪፖርት ኤርትራ ከጎረቤቶቿና ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ገንቢ በሆነ መልኩ እየተነጋገረች መሆኑን ጠቁሟል። በተለይ ኤርትራ ከጅቡቲ ጋር ያላትን የድንበር ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት መወሰኗ ይበል የሚያሰኝ ጅምር መሆኑን አትቷል።
የጸጥታው ምክር ቤት በኒው ዮርክ ሲሰበሰብ በጉዳዩ ላይ ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሀፊ ሊን ፓስኮ ኤርትራ ወታደሮቿን ከአወዛጋቢው ድንበር ማስወጣቷንና አደራዳሪዋ ቃታር ወታደራዊ ታዛቢዎችን በቦታው ማስፈሯን አረጋግጠዋል።
“ኤርትራና ጅቡቲ የድንበር ውዝግባቸውን ለመፍታት በቃታር መንግስት አደራዳሪነት የወሰዷቸውን ወሳኝ እርምጃዎች እናደንቃለን። ዋና ጸሀፊው የተባበሩት መንግስታት እርዳታ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፤ ሊረዳ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፣” በማለት ሊን ፓስኮ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራ አምባሳደር አርአያ ደስታ ከጅቡቲ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ጉልህ እመርታ ነው ብለውታል። ነገር ግን የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለው ማእቀብ ፍትሃዊ አይደለም በማለት አቤቱታቸውን አሰምተዋል።
“ኤርትራ ለሰላምና ደህንነት ከፍተኛ አትኩሮት ትሰጣለች። በዚህ ምክንያት በአካባቢዋ በሚደረጉ ፍሬአማ ውይይቶች ትርጉም ባለው መልኩ ተሳትፎ እንዳታደርግ መታገድ የለባትም። ዘለቄታ ያለው ሰላምን በሚያመጡ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የኤርትራ ተሳትፎ መረጋገጥ አለበት፣” ብለዋል አምባሳደር አርአያ ደስታ።
“ከጅቡቲ ጋር በቃታር መንግስት ሸምጋይነት ያገኘናቸው የዲፕሎማሲ ፍሬዎችን ማጤን ያስፈልጋል። በሶማሊያ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የምናደርገውን ጥረትም ተመልክቶ የጸጥታው ምክር ቤት የጣለብንን መአቀብ እንዲያነሳ እንጠይቃለን።”
በአስተርጓሚ የተናገሩት የጅቡቲ ተወካይ ካድራ አህመድ ሃሰን በኤርትራ ላይ የተጣለው ማእቀብ የሰላም ውይይት እንዲጀመር በር ከፍቷል ብለዋል።
“የተያዘው ጥረት አበረታች ቢሆንም፤ ረጅም መንገድ ይጠብቀናል። በሚቀጥሉት ወራት በሁለታችንም በኩል ቀጣይነት ያላቸው ስራዎችን መስራት ይጠበቃል። የተወያየንባቸው ነጥቦች በእጅጉ ወሳኝ ናቸው፤ የምርኮኞች ጉዳይ፣ የጠፉ ሰዎች ጉዳይና ድንበሩን በካርታ አስምሮ በምድር በችካል እስከመከለል ይሄዳል።”
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ባን ጊ-ሙን ቢሮ ያወጣው ሪፖርት ኤርትራ የጀመረቻቸውን ጥረቶች አበረታች ናቸው ቢልም፤ የጸጥታው ምክር ቤት ማእቀቡን ሲጥል ያስቀመጣቸውን ሁኔታዎች ለማሟላት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት ጠቁሟል።
ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤርትራ መልካም ጅምሮቿን የሚያበረታቱ ምላሽ ብታገኝም ከዩናይትድ ስቴይትስ በኩል ግኝ ተጨማሪ ጫና እንዲደረግ የህግ አውጭዎች እየወተወቱ ነው።
በዩናይትድ ስቴይትስ የህግ አውጭ ክፍል ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት ኮንግረስማን ኤድ ሮይስ ኤርትራ አሸባሪዎችን ከሚረዱ አገሮች ጥቁር መዝገብ ውስጥ እንድትገባ ጠይቀዋል።
ኮንግረስ ማን ሮይስ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን በጻፉት ደብዳቤ በዩጋንዳ መዲና ካምፓላ ሀምሌ 4 ቀን የደረሰውን ፍንዳታ ያቀነባበሩ የአል-ቃይዳ አጋሮች ጋር ይሰራል ያሉት የኤርትራ መንግስት ላይ ጫና እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አል-ሸባብ የተባለ የአሸባሪዎች አንጃ በዩጋንዳ ለ76 ሰዎች ህይወት መጥፋት መንስኤ የሆኑትን ጥቃቶች ማከናወኑን አስታውቋል። ድርጊቱም የተከናወነው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፈው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል አብዛሀኛው ወታደሮች ከዩጋንዳ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ነው።
ታዲያ በኮንግረሱ የሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው የጸረ-ሽብርተኝነት፣ የጸረ-ኑክሌር ግንባታና የንግድ ንኡስ ኮሚቴ ተሰሚነት ያላቸው ኮንግረስማን ሮይስ በጻፉት ደብዳቤ “ኤርትራ ለአልሸባብ የምትሰጠው ድጋፍ በአግባቡ በመረጃ የተረጋገጠ ነው” ሲሉ አልሸባብ በአሜሪካ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
ኤርትራ አሸባሪዎችን ከሚደግፉት አገሮች መካከል ከተፈረጀች ከኩባ፣ ኢራን፣ ሱዳንና ሶሪያ ጋር ትቀላቀላለች። በእነዚህ አገሮች የተጣሉ የዲፕሎማቲክ፣ ኢኮኖሚና የጦር መሳሪያ ማእቀቦች በኤርትራ ላይ ሊጫኑባት ይችላሉ።
ኤርትራ ለሶማሊያ ሸምቅ ተዋጊዎች እርዳታ ትሰጥ እንደነበረ መረጃዎች አሉ። ነገር ግን በናይኖቢ የInternational Crisis Group ስራአስኪያጅ E.J. Hogendoorn ኤርትራ የኢትዮጵያን ወታደሮች ይዋጉ ለነበሩ ሸማቂዎች እርዳታ መስጠቷ ቢታወቅም፤ በቀጥታ ለአሸባሪዎቹ የአል-ሸባብ ተዋጊዎች የምታደርገው እርዳታ የለም ይላሉ።
“በዚህ ጊዜ ኤርትራ አል-ሸባብን እንደምትረዳ የሚያሳይ ትንሽ እንኳን ማረጋገጫ አልተገኘም። በሶማሊያ የነበረውን የኢትዮጵያን ጦር በእጅ አዙር የሚወጉ ሀይሎችን ታስታጥቅ እንደነበረ መረጃ አለ። ያሉን መረጃዎች የሚጠቁሙት ኤርትራ ሂዝቡል-ኢስላምን እንጂ አል-ሸባብን አትደግፍም።
የሂዝቡል ኢስላም እንቅስቃሴዎች በእርግጥ አሳሳቢ ናቸው። ነገር ግን ሂዝቡል ኢስላም በቀጥታ በጎረቤት አገሮች ላይ የሽብር ጥቃቶችን ማቀነባበሩን የሚያሳዩ መረጃዎች የሉም።”
ሂዝቡል ኢስላም ከአል-ሸባብ ጋር ግንባር ፈጥሮ አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የሶማሊያ መንግስት ይወጋል። ሁለቱ ቡድኖች በሶማሊያ እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም ይንቀሳቀሱ እንጂ አብዛሃኛውን የሶማሊያ አካባቢዎች የሚያስተዳደረው አል-ሸባብ ነው።
አልሸባብ በዩናይትድ ስቴይትስ ጥቅሞች ላይ ከዚህ በፊት ይዝት እደነበር የገለጹት በናይኖቢ የInternational Crisis Group ስራአስኪያጅ E.J. Hogendoorn እሳካሁን ድርጅቱ ከዩናይትስ ስቴይትስ ጥቅሞች ይልቅ የምስራቅ አፍሪካ አገሮችን ሰላምና ጸጥታን በማወክ ረገድ አፍራሽ ሚና መጫወቱን ይገልጻሉ።